ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24, 2014 በጨረፍታ
አበይት አሃዝ
- አክሌድ ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24, 2014 ዓ.ም ድረስ 93 የተደራጁ የፖለቲካ የግጭት ኩነቶች እና 1,110 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾችን መዝግቧል።
- በተደራጀ የፖለቲካ ግጭት ምክንያት ከፍተኛው ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር በኦሮሚያ ክልል የተመዘገበ ሲሆን 821 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ተመዝግበዋል። የሶማሌ ክልል በ214 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ቁጥር በሁለተኝነት ይከተላል።
- ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ተደጋግሞ የተከሰተው የኩነት አይነት ጦርነት ሲሆን 50 ኩነቶች ከ852 ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር ጋር ተመዝግበዋል። በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች በ41 ኩነቶች እና 254 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ቁጥር በሁለተኝነት ይከተላል።
አበይት ክንውኖች
- ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ከመንግስት ታጣቂዎች – ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል፣ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከቀበሌ ታጣቂዎች – ጋር በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ውጊያ ማድረጉን ቀጥሏል።
- በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ቀጥለዋል። ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በቄሌም ወለጋ ዞን በሃዋ ገላን ወረዳ ለምለም ቀበሌ በመንደር 20 በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሌላ ከፍተኛ የሟቾች ቁጥርን ያስመዘገበ ጥቃት ተመዝግቧል። ይህ ጥቃት የተፈፀመው በምዕራብ ወለጋ ዞን በቶሌ ከ338 ያላነሱ የአማራ ተወላጆችን ህይወት የቀጠፈው ጥቃት በተከሰተ በሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ነው።
- ባለፈው ወር በሶማሌ ክልል አልሸባብ እና የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ተዋግተዋል።
- ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በአማራ ክልል በኦሮሚያ ልዩ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢዎች ሌላ ዙር ውጊያ ተቀስቅሷል።
በዚህ ሪፖርት ውስጥ
- ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24, 2014 የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
- ወርሃዊ ትኩረት፡ የፓንዶራ ሳጥን በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ተከፍቷል?
ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24, 2014 የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ወር በአማራ፣ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች የጦርነት ኩነቶች ተመዝግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። አብዛኛው የጦርነት ኩነቶች የተመዘገቡት በኦሮሚያ ክልል ሲሆን 36 ኩነቶች የተመዘገቡ ሲሆን ከባለፈው ወር ማለትም ከግንቦት 24, እስከ ሰኔ 23, 2014 ዓ.ም ውስጥ ከተመዘገቡ የጦርነት ኩነቶች ጋር ሲነፃፀር ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የተመዘገቡ የጦርነት ኩነቶች የ33 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል። በኦሮሚያ ከአንድ የጦርነት ኩነት በስተቀር የተቀሩት የጦርነት ኩነቶች የኦነግ-ሸኔን እና የመንግስት ኃይሎችን – ማለትም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል፣ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የቀበሌ ታጣቂዎችን ያሳትፉ ናቸው። ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጦርነት ኩነት ነበረው በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ነበር። ውጊያዎች በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ በምስራቅ ሸዋ፣ በፊንፊኔ ልዩ፣ በጉጂ፣ በቀለም ወለጋ፣ በሰሜን ሸዋ እና በምዕራብ ሸዋ ዞኖችም ተመዝግበዋል።
በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችም ቀጥለዋል (በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ ስለሚደርሰው ጥቃት የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ወርሀዊ: ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 23, 2014 ይመልከቱ)። ልክ እንደባለፈው ወር፣ ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በደረሰ ጥቃት ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር በኦሮሚያ የተመዘገበ ሲሆን 32 ኩነቶች ከ231 ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር ጋር ተመዝግበዋል። ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር በቄሌም ወለጋ ዞን በሃዋ ገላን ወረዳ ለምለም ቀበሌ በመንደር 20 የተመዘገበ ሲሆን ይህም ሰኔ 27 ቀን ኦነግ-ሸኔ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በማድረስ በትንሹ 150 የአማራ ተወላጆች የሆኑ ሰዎች መገደላቸውን እና ከ45 በላይ የሚሆኑ መቁሰላቸው ተነግሯል። አማፂ ቡድኑ ግን ይህን ጥቃት እንዳልፈፀመ ያስተባባለ ሲሆን የአካባቢው የመንግስት ታጣቂዎች ጥቃቱን ፈፅመዋል ሲል ከሷል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሰኔ 28, 2014፤ ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከሰኔ 25 እስከ ሐምሌ 1, 2014ን ይመልከቱ)።
በኦሮሚያ ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ አብዛኛው በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች ማለትም 68 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾችን ያሰከተሉ 26 ኩነቶች በመንግስት ታጣቂዎች – ማለትም በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በኦሮሚያ፣ በሶማሌ እና አማራ ክልል ልዩ ኃይሎች የተፈፀሙ ናቸው። እነዚህ ኩነቶች የተመዘገቡት በአርሲ፣ በባሌ፣ በምስራቅ ሸዋ፣ በምስራቅ ወለጋ፣ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ በምዕራብ አርሲ፣ በምዕራብ ሀረርጌ፣ በምዕራብ ሸዋ እና በምዕራብ ወለጋ ዞኖች ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ኩነቶች የተከሰቱት በምስራቅ ወለጋ ዞን ነው። አብዛኛዎቹ ተጎጂዎች ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ወይም የአማፂ ቡድኑን አባላት በመደበቅ ተከሰው ነበር።
በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ላይ በምትገኘው በባሌ ዞን በጉራዳሞሌ ወረዳ የድንበር ውዝግብ ተቀስቅሷል። ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ከሶማሌ ክልል የመጡ የሶማሌ ብሔረሰብ ታጣቂዎች በጉራዳሞሌ ወረዳ በተለያዩ ቦታዎች በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ቢያንስ ሁለት ጊዜ ጥቃት አድርሰዋል። በተጨማሪም ሐምሌ 21 ቀን የሶማሌ ክልል ኃይሎች በባሌ ዞን በጉራዳሞሌ ወረዳ በሃብሮና ቀበሌ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ተኩስ በመክፈታቸው ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች መሞታቸው ታውቋል። በእነዚህ ጥቃቶች ከ8,000 በላይ ንጹሃን ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ለመሰደድ ተገደዋል (የኢትዮጵያ ሪፖርተር፣ ሐምሌ 27, 2014)።
ኦነግ-ሸኔ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በተከሰቱት ክስተቶች ላይም ተሳትፏል። ባለፈው ወር አክሌድ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ስድስት የጥቃት ኩነቶችን ከ14 ሪፖርት ከተደረጉ የሟቾች ቁጥር ጋር መዝግቧል። ከአንድ የጥቃት ኩነት በስተቀር የተቀሩት ጥቃቶች በኦነግ-ሸኔ የተፈጸሙ ሲሆን በአጠቃላይ 10 ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል። አብዛኞቹ ጥቃቶች የተፈጸሙት በአማሮ ልዩ ወረዳ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ልዩ ኃይል በደራሼ ልዩ ወረዳ ጉማይዴ ሃይሌኛ ቀበሌ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ባልታወቀ ምክንያት ባደረሰው ጥቃት አራት አርሶ አደሮች ሲገደሉ ሁለት ሰዎች ቆስለዋል።
በአማራ ክልል ከሐምሌ 3 እስከ 4 በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ አጣዬ ከተማ አቅራቢያ በሚገኙት በርሀ ስላሴ፣ አርሶ አምቦ (ዘምቦ) እና ወይኗ ቀበሌዎች እና በኦሮሚያ ልዩ ዞን በጅልዬ ጥሙጋ ወረዳ ቤተ ቀበሌ የመንግስት ኃይሎች እና የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች እንደሆኑ የተጠረጠሩ ታጣቂዎች ተዋግተዋል ። የክልሉ ልዩ ኃይል እና የፌዴራል ኃይሎች ውጊያውን ለመቆጣጠር ወደ ስፍራው አቅንተዋል (ለበለጠ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ: ሐምሌ 2-8, 2014 ይመልከቱ)።
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ሐምሌ 4 ቀን የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ልዩ ኃይል እና የክልሉ ፖሊስ የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) አባላት ጋር በካማሺ ዞን ምዥጋ ወረዳ ደዴሳ ቀበሌ ከተዋጉ በኃላ ቀበሌውን ተቆጣጥረዋል። ጉህዴን ይህንን ቀበሌ እና በምዥጋ ወረዳ የሚገኙ ሌሎች አምስት ቀበሌዎችን በግንቦት 2013 ተቆጣጥሮ ነበር። በተጨማሪም በክልሉ በሶስት ሰዎች ላይ ሞት ያስከተሉ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ሁለት ጥቃቶች ተመዝግበዋል። ሐምሌ 3 ቀን በመተከል ዞን ዳንጉራ ወረዳ በብርቱካን እና በሲሳይ መንደር የፋኖ ታጣቂዎች ሁለት የአገው ብሔረሰብ አባላትን በጥይት መግደላቸው ተነግሯል። ሐምሌ 6 አካባቢ በመተከል ዞን በድባጤ ወረዳ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንደሆኑ የተገመቱ የመንግስት ታጣቂዎች አንድ የጉህዴን አባልን ተኩሰው ገድለዋል። ይህ ሰው ወደ ከተማዋ የገባው ጉህዴን ከመንግስት ጋር እንዲደራደር የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ነው።
በመጨረሻም ባለፈው ሐምሌ ወር ላይ አልሸባብ እና የኢትዮጵያ ጦር በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እና በሶማሊያ የድንበር አካባቢ በርካታ ቦታዎች ላይ ተዋግተዋል። ሐምሌ 7 ቀን የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ከአልሸባብ ታጣቂዎች ጋር በአፍዴር ዞን በኤልቃሬ-ሴረር ወረዳ ቡላ ተራራ አካባቢ በመዋጋት የአልሸባብ አዛዥን ገድለዋል። ከሳምንት በኋላ ሐምሌ 13 ቀን አልሸባብ በሶማሊያ በዬድ እና አቶ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ካምፖች ላይ ጥቃት በመሰንዘሩ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ውጊያ ተቀስቅሷል። በአፍዴር ዞን በሁልሁል በአልሸባብ እና በክልሉ ኃይሎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል ውጊያ እስከ ሐምሌ 16 ድረስ ቀጥሏል። ሁለቱ ወገኖች ሐምሌ 18 ቀንም በሸበሌ ዞን በፌርፈር ወረዳ አል ኩዱን አካባቢ ተዋግተዋል (ስለነዚህ ውጊያዎች የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ሐምሌ 9-15, 2014 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ: ሐምሌ 16-22, 2014 ይመልከቱ)።
ወርሃዊ ትኩረት፡ የፓንዶራ ሳጥን በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ተከፍቷል?
ባለፈው ወር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከዘጠኝ ክልሎች ለምክር ቤቱ የቀረቡ ከ30 በላይ ራስን በራስ የማስተዳደር እና የማንነት ጥያቄዎችን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል። ከእነዚህ 30 ጥያቄዎች ውስጥ 24ቱ ራስን በራስ ከማስተዳደር ጋር የተያያዙ ናቸው። በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔው “በክልሉ ህዝቦች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ነው” ሲል አመልክቷል (ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሐምሌ 7, ቀን 2014)። ይህን ተከትሎ አዲስ መዋቅር ሊካሄድ ነው በሚል ለተነሳው ውጥረት የጸጥታ ኃላፊዎች የጉራጌ እና ጌዲዮ ዞኖች ነዋሪዎችን ሰልፎች ወይም ብጥብጥ የሚያነሳሳ ድርጊት እንዳያደርጉ አስጠንቅቀዋል። በሐምሌ ወር የፌዴራል የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል እና የክልሉ መንግስት የጌዲኦ ዞን ብቻውን ክልላዊ መንግስት ለመመስረት ባቀረበው ጥያቄ ምክንያት በጌዲኦ ዞን ሁከት ለመፍጠር አሲረዋል ያሏቸው ያልታወቀ ቡድን ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠንቅቀዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ሐምሌ 8 , 2014)። ሐምሌ 26 ቀን የደቡብ ክልል የጸጥታ ኃላፊዎች መንግስት “የጉራጌ ዞን የመዋቅር ጥያቄን ሽፋን በማድረግ ህገወጥ እና መደበኛ ያልሆኑ ድርጊቶችን እንደማይታገስ አስጠንቅቀዋል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ሐምሌ 29, 2014)። ሐምሌ 29 ቀን በጉራጌ ዞን ቡኢ ከተማ ኮማንድ ፖስት የተቋቋመ ሲሆን ማንኛውም ሰው አዲስ የታቀደውን የክላስተር ክልል የሚቃወም ምልክት እንዳይይዝ ወይም እንዳይለብስ ከልክሏል (ትክቫህ ኢትዮጵያ፣ ሐምሌ 29, 2014)። የወልቂጤ ከተማ እንደ አዲስ የቀረበውን የጉራጌ ዞን መዋቅር እና አዲስ የክላስተር ክልል መመስረትን ያልተቀበሉት ነዋሪዎች “የተለመደ እንቅስቃሴን ባለማድረግ” እና በከተማዋ ሰልፍ በመውጣት “ክላስተር የለም” የሚሉ መፈክሮችን በማሰማት ቅሬታቸውን ገልፀዋል (አዲስ ስታንዳርድ ነሐሴ 3, 2014)።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራቲክ ሪፕብሊክ (ኢፌዲሪ) ሕገ-መንግስት አንቀፅ 39 መሠረት ማንኛውም ብሔረሰብ የራሱን ክልል የመመስረት መብት አለው። ይህን የሚያሟሉ ቡድኖች የሚያቀርቡት የራስን ክልል የመመስረት ጥያቄ በሚመለከተው የታችኛው ምክር ቤት እርከን መፅደቅ ያለበት ሲሆን ይህ የፀደቀው ውሳኔም በጽሁፍ ለክልሉ ምክር ቤት መቅረብ አለበት። ይህ የጽሁፍ ጥያቄ በቀረበ በአንድ አመት ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ መደረግ አለበት (የኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት፣ አንቀፅ 47)። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ እንዲህ ያለውን ጥያቄ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ማሳካት የቻለው የመጀመሪያው ብሔረሰብ ሲዳማ ሲሆን በህዳር ወር 2012 የሲዳማ ክልል ከደቡብ ክልል ተለያይቷል። እንደ ወላይታ እና የጉራጌ አይነት በርካታ የራስን ክልል የመመስረት ጥያቄዎች በክልል እና በፌዴራል ደረጃ ከፍተኛ ባለስልጣናት ችላ ተብለዋል ወይም ዘግይተዋል።
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የተቋቋመው በ1980ዎቹ ነው (ለበለጠ መረጃ የኢፒኦን የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ገፅ ይመልከቱ)። ሃምሳ ስድስት ብሔረሰቦች “የክልሉ ብሔረሰቦች” ተብለው በመንግስት እውቅና ተሰጥቷቸዋል (ቤዛ ደስአለኝ እና ንጉሴ አፈሻ፣ ታህሳስ 2011)። በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እንደ ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ከፋ፣ ሃዲያ፣ ጌዲኦ እና ጉራጌ ያሉ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ህገ መንግስቱን መሰረት አድርገው የየራሳቸው ክልል ለመመሥረት ለዓመታት ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ሌሎች ልክ እንደ ሰገን አካባቢ ሚኖሩ ደግሞ የራሳቸውን ዝቅ ያለ የራስ አስተዳደር (ዞን፣ ወረዳ፣ ልዮ ወረዳ) ለማቋቋም ጠይቀዋል (ለበለጠ መረጃ የኢፒኦን የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ግጭት ገፅ ይመልከቱ)። የቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የሚመራው መንግስት እነዚህን ጥያቄዎች ጸጥ ለማሰኘት የኃይል እርምጃ በመውሰድ አዳዲስ ክልሎች መመስረትን የሚደግፉትን አስሯል። ነገር ግን በ2012 በሲዳማ በተካሄደው ስኬታማ ህዝበ ውሳኔ እና ክልል መሆን ሌሎች በርካታ ብሔረሰቦችም ተመሳሳይ እጣ ፈንታን ለመከተል ተስፋ እንዲያደርጉ አድርጏቸዋል። ጉራጌ፣ ወላይታ፣ ዳውሮ፣ ጎፋ፣ ጌዲኦ፣ ከፋ፣ ጋሞ፣ ከምባታ-ጠምባሮ፣ ቤንች-ማጂ፣ ሀዲያ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች ጥያቄያቸውን በየዞን ምክር ቤቶቻቸው አፀድቀው ይህን የፀደቀ ውሳኔያቸውን ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት አቅርበዋል (ኢትዮጵያ ኢንሳይት፣ ሐምሌ 30, 2013)።
ብዙ የክልሎች/የዞን ጥያቄዎች በመነሳታቸው፣ አብይ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ለሚነሱት የራስ አስተዳደር ጥያቄዎች የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማቅረብ የባለሙያዎች ቡድን ሾመዋል። ባለሙያዎቹ ሶስት አማራጮችን አቅርበዋል፤ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እንዳለ እንዲቀጥልና በክልሉ ምክር ቤት መቀመጫዎች ላይ ግን ለውጥ እንዲደረግ፣ ሲዳማ የራሱን ክልል ከመሰረት በኃላ የተቀሩትን የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል አድርጎ መቀጠል ወይም ክልሉን በአምስት “የክላስተር” ክልሎች እንዲከል ማድረግ የሚሉ ነበሩ (ሪፖርተር ጋዜጣ፣ ሐምሌ 30, 2014)። ባለፈው ወር የፌዴራል መንግስት ክላስተር ክልሎች እንዲቋቋሙ ሀሳብ ያቀረበ ሲሆን ይህም የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልልን ለሦስት ትናንሽ ክልሎች የሚከፍል ነው። እነዚህ ክላስተር ክልሎች ከአንድ የተወሰነ ብሔረሰብ ይልቅ በርካታ ዞኖችን እና ልዩ ወረዳዎችን ያቀፉ ናቸው። በዚህ ሃሳብ መሰረት 11ኛው ክልል – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል – ህዝበ ውሳኔ ተከትሎ በህዳር 2013 ተመስርቷል። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በአምስት ዞኖች – ምዕራብ ኦሞ፣ ቤንች ሸኮ፣ ከፋ፣ ዳውሮ እና ሸካ ዞኖች – እና በአንድ ልዩ ወረዳ – ኮንታ ልዩ ወረዳ 12 ብሔረሰቦችን ያቀፈ ነው።
በሐምሌ ወር የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሁለት ክላስተር ክልሎች እንደሚከፈል ዘገባዎች አመላክተዋል። አሁን ያለው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል 11 ዞኖች እና ስድስት ልዩ ወረዳዎችን ያቀፈ ነው። በአዲሱ አደረጃጀት መሰረት የመጀመሪያው ክላስተር ክልል ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች – ወላይታ፣ ጌዲዮ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ እና ኮንሶ ዞኖች እንዲሁም አማሮ፣ ባስኬቶ፣ ቡርጂ፣ ደራሼ እና አሌ ልዩ ወረዳዎችን ያቀፈ ይሆናል። ሁለተኛው ክላስተር ክልል አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ – ሀዲያ፣ ከምባታ፣ ሀላባ፣ ጉራጌ እና ስልጤ ዞኖች እና የም ልዩ ወረዳን ያቀፈ ይሆናል። ሃሳቡ ከተሳካ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሚባል አይኖርም ማለት ነው። ከጉራጌ ዞን ምክር ቤት በስተቀር ቀሪዎቹ 10 የዞኖች እና ስድስት ልዩ የወረዳ ምክር ቤቶች ሐምሌ 23 እና 24 አዲስ ክላስተር ክልሎችን ለመቀላቀል ወስነው ድምጽ ሰጥተዋል። የእነዚህ ምክር ቤቶች ውሳኔ የሁለቱን ክላስተር ክልሎች የማደራጀት ሂደት በይፋ ለመስጀመር ውሳኔውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርበዋል (የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ሐምሌ 28, 2022)። ይህ ውሳኔ ከፀደቀ በኢትዮጵያ 12 ክልሎች ይኖራሉ ማለት ነው። አንዳንድ ብሔር ብሔረሰቦች በተለይም እንደ ጉራጌ፣ ጌዲዮ እና ወላይታ ያሉ የየራሳቸውን ክልል ለመመስረት ጥያቄ ያቀረቡ ወገኖች በቅርቡ በቀረበው የክላስተር ክልል ላይ ቅሬታቸውን የገለፁ ሲሆን ሕገ መንግሥታዊ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄያቸው እንዳልተመለሱላቸው ገልፀዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሐምሌ 15, 2014፤ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ ነሐሴ 10, 2014፤ ኢኤምኤስ፣ ሐምሌ 9, 2014)።
የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ለእያንዳንዱ “ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች” “የራስን ዕድል በራስ የመወሰን፣ እስከ መገንጠል መብትን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መብት” በመስጠቱ ልዩ ነው። ጠያቂው ቡድን እውቅና ያለው የብሔር ማህበረሰብ መሆን እንዳለበት እንጂ በህገ መንግስቱ የተገለጹ ኢኮኖሚያዊ፣ ስነ-ህዝብ ወይም ሌሎች መመዘኛዎች እንደዚህ አይነት ጥያቄዎች ከመነሳታቸው በፊት ሊሟሉ የሚገባቸው መስፈርቶች አይደሉም። በተጨማሪም ከደርግ (ወታደራዊ ጁንታ) ማርክሲስት-ሌኒኒስት ርዕዮተ ዓለም የተወረሰው የኢትዮጵያ የመሬት ስርዓት “የገጠርና የከተማ መሬት እንዲሁም የሁሉም የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት… ለመንግስት እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ የተሰጠ ነው” (የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት፣ አንቀጽ 40)። አስተዳደራዊ ውድድሮች እና የ’ክልላዊ’ ወይም የ’ዞን’ ጥያቄዎች የአካባቢ ሊሂቃን በየብሔረሰባቸው የሚነሱትን ሀብቶች እንደ የራስ ገዝ አስተዳደር የበለጠ ለመቆጣጠር የሚያደርጉት ተደርጎ ሊታይ ይችላሉ። ይህንን አመክንዮ በመጠቀም፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች ክልል ውስጥ ያሉ አንዳንድ ትናንሽ አካባቢዎችን ጨምሮ የአካባቢ አስተዳዳሪዎች በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ለክልል አስተዳዳሪዎች የሚሰጠውን ጥቅም ማግኘት ይችላሉ። ከ2010 በፊት የክልል ወይም አዲስ የዞን አደረጃጀት ጥያቄዎች በፀጥታ ኃይሎች በኃይል ተዳፍነዋል። የአብይ አስተዳደር ለእነዚህ ጥያቄዎች ነፃነት በማሳየቱ እንደ ደቡብ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች ክልል ብዙ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በሚኖሩበት ቦታ የአስተዳደራዊ ጥያቄ ፓንዶራ ሳጥን ተከፍቷል።
ከእነዚህ ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ ረብሻም ተከስቷል። ከታህሥስ 2014 ጀምሮ በአክሌድ በደቡብ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች ክልል የተመዘገቡ አብዛኛው የፖለቲካ አለመረጋጋት ኩነቶቶች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች፣ አዲስ ድንበሮች፣ ወይም አዲስ ከተፈጠሩ ዞኖች መካተት/መገለል ጋር የተያያዙ ናቸው። በሚያዝያ ወር በደቡብ ኦሞ ዞን አሪ ወረዳ እና ጂንካ ከተማ ውስጥ ለአሪ ብሔረሰብ የተለየ የዞን አስተዳደር እንዲቋቋም የጠየቁ የአሪ ብሔረሰብ ወጣቶች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በማድረስ አንዳንድ ቤቶችን አቃጥለዋል። የደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት የአሪ ብሔረሰብ ጥያቄዎችን በአጀንዳነት በስብሰባዉ ላይ ለዉይይት ባለማቅረቡ የሁከቱ መንስኤ ሆኗል። የአሪ ብሔረሰብ በአሁኑ ወቅት ከሌሎች 16 ብሔረሰቦች ጋር በደቡብ ኦሞ ዞን ስር እየተስተዳደረ ይገኛል። የአሪ ብሔረሰብ አባላት የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር ዋና ከተማ የሆነውን ጂንካ ከተማን በማካተት የራሳቸውን የዞን አስተዳደር ማቋቋም ይፈልጋሉ። በተመሳሳይ በሚያዝያ 2014 በደራሼ ልዩ ወረዳ እና በኮንሶ ዞን ለሳምንታት የዘለቀው አለመረጋጋት የደራሼ ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪን እና ሌሎች አራት ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጨምሮ የበርካታ ንፁኃን ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ሐምሌ 4, 2014; እንዲሁም ስለእነዚህ ክስተቶች የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ወርሀዊ: ከመጋቢት 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ይመልከቱ)። በሐምሌ 2014 አዲስ አስተዳደር እስኪ ሰየም ድረስ ወረዳው ለወራት ያህል በፀጥታ ኃይሎች እየተተዳደር ነበር (ቪኦኤ አማርኛ፣ ሐምሌ 4, 2014)።
በመጪዎቹ ወራት በደቡብ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች ክልል አዲስ በታቀዱት ክላስተር ክልሎች ውስጥ በሚገኙ አካባቢዎች ወይም አዋሳኝ አካባቢዎች ብጥብጥ የመቀጠል እድሉ ከፍተኛ ነው። የታቀዱት አዲስ ክልሎች ሊፈጠሩ የሚችሉ የአመጽ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የፖለቲካ ልምድም ሆነ የጸጥታ አማራጭ ላይኖራቸው ይችላል። ይህ በተለይ ነሐሴ 5 ቀን 40 የጉራጌ የዞን አባላት አዲስ የታቀደውን ክላስተር ክልል በመደገፍ እና 52 የዞኑ አባላት ደግሞ አዲስ የታቀደውን ክላስተር ክልል በመቃወማቸው በአብዛኛው የዞኑ ምክር ቤት አባላት ውድቅ በተደረገበት ጉራጌ የዞን ሊከሰት ይችላል። ነገር ግን ነሐሴ 7 ቀን በጉራጌ ዞን ከሚገኙት ስድስት ወረዳዎች እና ሁለት የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች አራት ወረዳዎችና አንድ የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች አዲስ የታቀደውን ክላስተር ክልል ለመቀላቀል ድምጽ ሰጥተዋል። የከተማ እና የወረዳ ምክር ቤቶቹ እንዲሁም የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ውሳኔያቸውን ነሐሴ 9 ቀን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርበዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ነሐሴ 9, 2014፤ ዲደብሊው አማርኛ፣ ነሐሴ 9, 2014)። ይህ እንደነዚህ ያሉ ጥያቄዎች በቅድሚያ ለዞኑ ምክር ቤት ከዚያም ለክልሉ ምክር ቤት መቅረብ አለባቸው የሚለው በሕገ-መንግስቱ ላይ ከተዘረዘሩት የአሠራር ስርዓቶች ጋር የሚቃረን አካሄድ ነው። በጉራጌ ዞን ሊደረግ የታቀደውን መዋቀር መንግስት እንዴት እንደሚያስፈፅመው ግልፅ አይደለም። የጌዲኦ ዞን አስተዳደር የታቀደውን ክላስተር ክልል ለመቀላቀል ቢስማማም የጌዲኦ ዞን ነዋሪዎች ግን በአዲሱ አደረጃጀት የተሰማቸውን ቅሬታም ገልፀዋል (ኢኤምኤስ፣ ሐምሌ 9, 2014)። በወላይታ ዞንም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሐምሌ 25, 2014፣ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ ነሐሴ 10, 2014)። አዲስ የቀረበው አደረጃጀት በደቡብ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች ክልል የሚገኙ የተለያዩ ብሔረሰቦችን ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች ለማስቆም የሚያስችል ማረጋጋጫ ስለማይሰጥ እንደዚህ ያሉ ጥያቄዎችን አዲስ የቀረበው አደረጃጀት ምላሽ እንደሚሰጥ ግልፅ አይደለም። በሕገ-መንግስቱ መሠረት ራስን በራስ ለማስተዳደር ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የቀረበው የመዋቅር ሂደት በኢትዮጵያ ውስጥ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ከድንበር ለውጦች ጋር የተያያዘ ግጭት ብዙ ጊዜ ይከሰታል። የኢፒኦ ተመራማሪዎች እነዚህን ጉዳዮች ዙሪያ ያሉ አዳዲስ መረጃዋችን በጥንቃቄ በመከታተል ያቀርባሉ።