በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 –ህዳር 2, 20151እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 3,599
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 20,407
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 9,058
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከጥቅምት 26- ህዳር 2, 20152በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 23
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 93
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 47
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን በኢፒኦ የዳታ ፋይል እንዲሁም በዋናው የአክሌድ ኤክስፖርት መሳሪያ ውስጥ ማግኘት ይችላሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በሰሜን ኢትዮጵያ ምንም አይነት የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ያልተዘገቡ ሲሆን ይህም በቅርቡ የተፈረመው የሰላም ስምምነት የመጀመሪያ ስኬት መሆኑን ያመላክታል። ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) ኃይሎች ሀላፊዎች በኬንያ ናይሮቢ ተገናኝተው ከሳምንት በፊት በደቡብ አፍሪካ የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ተወያይተዋል። ከስድስት ቀናት የዝግ ውይይት በኋላ ህዳር 3 ቀን ሁለቱ ወገኖች ሌላ ሰነድ ተፈራርመዋል፡ “ለዘለቄታዊ ሰላም ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ የከፍተኛ አዛዦች መግለጫ” (የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ህዳር 3, 2015)።
የኦሮሚያ ክልል በሀገሪቱ ካሉ ክልሎች እጅግ ያልተረጋጋ ክልል እንደሆነ የቀጠለ ሲሆን በምዕራብ ኦሮሚያ ከፍተኛ የሆነ ግጭት ተዘግቧል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ግጭቱ የተባባሰ ሲሆን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ በበርካታ ዋና ዋና ከተሞች ላይ ጥቃት አድርሷል። ጥቅምት 27 ቀን ኦነግ-ሸኔ የምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደር ማዕከል በሆነችው ነቀምት ከተማ በመግባት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ጋር በከተማው በኩምሳ ሞረዳ፣ በማርያም ሰፈር፣ በቀበሌ ሰባት እና ደርጌ በኬ ጃማ አከባቢዎች ተዋግቷል። ቢያንስ አምስት የኦነግ-ሸኔ አባላት፣ ሶስት ሰላማዊ ሰዎች እና ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የመንግስት ኃይሎች ሲግደሉ ቁጥራቸው በውል ያልተገለጸ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። በተጨማሪም ቡድኑ ሁለት ባንኮችን ሲዘርፍ፣ እስረኞችን ፈትቶ ቁጥራቸው ያልታወቁ የመንግስት ባለስልጣናትን አፍኖ ወስዷል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ጥቅምት 30, 2015፤ ኢሳት፣ ጥቅምት 27, 2015፤ ኢኤምኤስ፣ ጥቅምት 27, 2015)። የኦነግ-ሸኔ ቃል አቀባይ ቡድኑ ወደ 120 የሚጠጉ እስረኞችን እንደፈታ ተናግረዋል (ትዊተር@ኦዳታርቢደብሊውቢኦ፣ ጥቅምት 27, 2015)።
ኦነግ-ሸኔ ብዙ ቦታዎችን ለመቆጣጠር እና የመንግስትን ይዞታ ለማስፈራራት ድፍረት የተሞላበት እርምጃዎችን እየወሰደ ይመስላል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት በምስራቅ ወለጋ ዞን ከሚገኙ 21 ወረዳዎች ውስጥ ታጣቂው ቡድን 11 ወረዳዎችን መልሶ በቁጥጥር ስር ማዋል ችሏል። እንደ የቶሌ ቀበሌ ምክትል ሊቀመንበር ኦነግ-ሸኔ በጊምቢ ወረዳ ውስጥ የሚገኙትን “32ቱንም ቀበሌዎች ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስችል መልኩ” እንደገና ተቆጣጥሮታል (የኢትዮጵያ ሪፖርተር፣ ጥቅምት 27, 2015)። በዚህም የተነሳ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የጸጥታ ኃይሎች እና በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ከእነዚህ አካባቢዎች እየተሰደዱ ይግኛሉ። ጥቅምት 25 ቀን በጊምቢ ወረዳ በቶሌ ቀበሌ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች የመንግስት ታጣቂዎች አካባቢውን ለቀው በወጡበት ወቅት በኦነግ-ሸኔ ድጋሚ ጥቃት እንዳይደርስባቸው በመስጋት አካባቢውን ለቀው መውጣታቸው ተዘግቧል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ እንደገለጸው ከ1,800 በላይ አባወራዎች በፌዴራል ፖሊስ ታጅበው አካባቢውን ለቀው ተሰደዋል (ቦርከና፣ ህዳር 2, 2015)። በሰኔ 2014 በቶሌ ቀበሌ የኦነግ-ሸኔ ኃይሎች እንደሆኑ የተጠረጠሩ ኃይሎች በደረስ ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ህይወት አልፏል (ለበለጠ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከሰኔ 11 እስከ 17, 2014 ይመልከቱ)።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሚያ ክልል የአየር ጥቃት የቀጠለ ሲሆን ይህ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጥቃት የኦነግ-ሸኔን ግስጋሴ ለማቀዝቀዝ ኦነግ-ሸኔ ላይ ያነጣጠረ ነው። ባለፈው ሳምንት ጥቅምት 30 ቀን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በምዕራብ ወለጋ ዞን መንዲ ውስጥ በኦነግ-ሸኔ መኪና ላይ ተደጋጋሚ የአየር ድብደባዎችን ያደረገ ሲሆን 16 ሰላማዊ ሰዎች ጨምሮ ቢያንስ 18 ሰዎች ተገድለዋል። ኦነግ-ሸኔ መንዲን የተቆጣጠረው በቅርቡ ነበር። ከመስከረም 2015 ጀምሮ በክልሉ የአየር ድብደባዎች ቁጥር ጨምሯል (በአገሪቱ ስላለው የአየር ድብደባ አዝማሚያ የበለጠ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ወርሀዊ: ከመስከረም 21 እስከ ጥቅምት 21, 2015ን ይመልከቱ)።
ላለፉት ጥቂት ሳምንታት ኦነግ-ሸኔ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ስር የሚገኘውን አሶሳ ዞን በነቀምት ከተማ አድርጎ ከአዲስ አበባ ጋር የሚያገናኘውን ዋና መንገድ ዘግቷል። ቡድኑ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ አሽከርካሪዎችን ወደ አሶሳ ሲያቀኑ አፍኖ መውሰዱ ታውቋል። እንደ አይን እማኞች ገለጻ ዋናው መንገድ በመዘጋቱ ምክንያት የከባድ መኪና እና የአውቶቡስ ሹፌሮችን ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎች በጊምቢ ከተማ ውስጥ ለመቆየት ተገደዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥቅምት 30, 2015)። በዚህም ምክንያት መሰረታዊ ፍላጎቶች እና እቃዎች ወደ ዞኑ መግባት ባለመቻላቸው በአካባቢው የዋጋ ጭማሪ ተከስቷል።
በኦነግ-ሸኔ ሌሎች ሁለት ተጨማሪ የአፈናዎችም በክልሉ ተመዝግበዋል። በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦራ ወረዳ ኦነግ-ሸኔ ጥቅምት 28 ቀን ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ አሽከርካሪዎችን አፍኖ ወሰዷል። በማግስቱ በምዕራብ ሸዋ ዞን ጊንጪ እና ጀልዱ መካከል ያለውን መንገድ ለሰአታት በመዝጋት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎችን አፍኖ ወስዷል። ካለፉት ጥቂት ሳምንታት ወዲህ ታፍነው የሚወሰዱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን አብዛኞቹ ጠላፊዎች የተጠለፉ ሰዎችን ለማስለቀቅ ገንዘብ እየጠየቁ ነው።
በተጨማሪም በክልሉ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርስው ጥቃት ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት 14 በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ የጥቃት ኩነቶች ተመዝግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ከእነዚህ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ከደረሱ ጥቃቶች መካከል አብዛኞቹ – ሰባት ኩነቶች – በኦነግ-ሸኔ አባላት ቡድኑ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ በምዕራብ ወለጋ ዞን በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የተፈፀሙ ናቸው። እነዚህ ጥቃቶች የተመዘገቡት በጊምቢ፣ ጨቆርሳ፣ ነጆ፣ ቂልጡ ካራ፣ ቢላ፣ ባቦ እና መንዲ ወረዳዎች ነው። በተጨማሪም በአርሲ ዞን በጀጁ ወረዳ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት የቀጠለ ሲሆን በአፍሪካ ጁስ ካምፓኒ፣ ሁሩታ ዶሬ ቀበሌ እና አምሻራ ቀበሌ ሦስት ጥቃቶች ተፈፅመዋል።
የተቀሩት ሦስት ጥቃቶች በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሸዋ፣ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ እና በምስራቅ ወለጋ ዞኖች ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች እና በአማራ ብሄር ታጣቂዎች የተፈፀሙ ናቸው።
ኦነግ-ሸኔ ኃይሉ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በሚያነጣጥሩ ድርጊቶች አለመሳተፋቸውን በየጊዜው ይገልጿል። ነገር ግን የአይን እማኞች እየተፈፀመ ላለው አፈና እና ለሌሎች የወንጀል ድርጊቶች ቡድኑን ተጠያቂ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። የኦነግ-ሸኔ ባለስልጣናት በአካባቢው “እነሱን በማስመሰል” እራሳቸውን ባደራጁ የታጠቁ ቡድኖች በሚፈፅሙት እንደ ለገንዘብ ሰዎችን ማገት ያሉ የኃይል እርምጃች በኦነግ-ሸኔ ስም በሚደረጉ ቡድኖች ላይ ያላቸውን ብስጭት ገልጸዋል።3ከኦነግ-ሸኔ ባለሥልጣን ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ፣ ሐምሌ 2014። እነዚህ ጥቃቶች በእርግጥ በኦነግ-ሸኔ ይፈፀሙም አይፈፀሙም የእንደዚህ አይነት ክስተቶች መብዛት አሳሳቢ እየሆነ ሲሆን የኦሮሚያ የፀጥታ ሁኔታ በአጠቃላይ እያሽቆለቆለ መምጣቱን ያሳያል። ይህ ክስተት በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ ተጨማሪ የመንግስት ኃይሎች ወደሌላ ቦታ መንቀሳቀስ በሚጀምሩበት ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ ሊለወጥ የሚችል ቢሆንም ይህ ለውጥ ግን በቅፅበት ሊሆን አይችልም።
በየካቲት 2014 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለፓርላማ አባላት ባደረጉት ንግግር ኦነግ-ሸኔ ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ በማግኘቱ የፌዴራል መንግስት ቡድኑን ለመቆጣጠር እየታገለ መሆኑን ከዚህ በፊት ብዙም ባልተለመደ መልኩ አምነው ገልፀው ነበር። ኦነግ-ሸኔ “ሌሊት የሚሰርቅ ነገር ካለ ዙሪያውን እንደሚያይ ሌባ” ነው ሲሉ “ሰዎች [የኦሮሞ ተወላጆች] ታጣቂዎችን በመደበቃቸው” ምክንያት “ወታደራዊ ስልት ብቻውን እንደማይሰራ” አምነዋል (ኢቢሲ፣ የካቲት 15, 2015)።
በሀገሪቱ ሌላ ስፍራዎች ሦስት የውጊያ ኩነቶች ተመዝግበዋል። በጋምቤላ ክልል ጥቅምት 30 ቀን ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሌ ብሄረሰብ ታጣቂዎች በአኝዋክ ዞን ዲማ ወረዳ ባንዴራ ቀበሌ ውስጥ በጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይል ላይ የደፈጣ ጥቃት ሰንዝረው የወረዳ ፖሊስ አዛዥን ጨምሮ ሁለት የክልሉ ፖሊስ አባላትን ገድለው አንድ ሌላ ሰው አቁስለዋል። ከአንድ ቀን በፊት ታጣቂዎቹ የሰላማዊ ሰዎችን መኪና በማስቆም ሊያደርጉት የነበርው ጥቃት ከከሸፈ በኃላ የመንግስት ኃይሎች የታጠቀውን ቡድን በማፈላለግ ላይ ነበሩ (ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥቅምት 30, 2015)።
በመጨረሻም በአፋር እና በሶማሌ ብሄረሰብ ታጣቂዎች መካከል ሁለት የውጊያ ኩነቶች በሶማሌ ክልል በሲቲ ዞን ደኸይሚድ ወረዳ እና ጃራር ዞን ደገሃመዶ ወረዳ የተመዘገቡ ሲሆን በእነዚህ ውጊያዎች ምክንያት18 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል። በደኸይሚድ ወረዳ ለተፈጠረው ግጭት መንስኤው በውል የማይታወቅ ሲሆን በደገሃመዶ ወረዳ ሁለቱ ወገኖች የተጋጩት በሲቲ ዞን በሚገኙ አወዛጋቢ (ክርክር ባለባቸው) ቦታዎች ምክንያት ነው። የአፋር እና የሶማሌ ብሄረሰብ ታጣቂዎች በሲቲ ዞን አወዛጋቢ በሆኑ ከተሞች ምክንያት አልፎ አልፎ ይጋጫሉ (ለበለጠ መረጃ የአፋር–ሶማሌ ድንበር ግጭት ገፅን ይመልከቱ)።