ከጥቅምት 22 እስከ ሕዳር 21, 2015 በጨረፍታ
አበይት አሃዞች
- አክሌድ ከጥቅምት 22 እስከ ሕዳር 21, 2015 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ 118 የተደራጁ የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች እና 477 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች መዝግቧል።
- በተደራጀ የፖለቲካ ግጭት ምክንያት ከፍተኛው ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር እና ኩነት በኦሮሚያ ክልል የተመዘገበ ሲሆን 112 ኩነቶች እና 447 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ተመዝግበዋል። የሶማሌ ክልል በ18 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ቁጥር በሁለተኝነት ይከተላል።
- ከጥቅምት 22 እስከ ሕዳር 21, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ተደጋግሞ የተከሰተው የኩነት አይነት ጦርነት ሲሆን 61 ኩነቶች ከ139 ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር ጋር ተመዝግበዋል። በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች በ48 ኩነቶች እና 253 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ቁጥር በሁለተኝነት ይከተላል።
አበይት ክንውኖች
- ከጥቅምት 22 እስከ ሕዳር 21, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል በተደራጀ የፖለቲካ ግጭት ምክንያት የተመዘገቡ ኩነቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ የጨመሩ ሲሆን ይህም በሰኔ 2014 ከተመዘገቡት 74 ኩነቶች ከፍ ብሎ በዚህ ወር 112 ኩነቶች ተመዝግበዋል።
- ከኦሮሚያ ክልል ጋር ሲነፃፀር ከጥቅምት 22 እስከ ሕዳር 21, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በመላ አገሪቱ የተዘገቡት የፖለቲካ ግጭቶች ስድስት ብቻ ናቸው።
- በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ምክንያት በትግራይ ክልል የሚከሰቱ ግጭቶች በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሰዋል። በኤርትራ ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎችን መግደል፣ ዘረፋ እና ማፈናቀልን ያካተቱ የተኩስ አቁም ጥሰት በትግራይ ክልል መፈፀሙ ተነግሯል።
- በኦሮሚያ ክልል በነበረው ውጊያ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሽኔን፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይልን፣ የአማራ ብሔር ታጣቂዎችን፣ የፋኖ ታጣቂዎችን እና የኦሮሞ ቀበሌ ታጣቂዎችን ጨምሮ የተለያዩ አካላት የተሳተፉበት ነበር።
- በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃትም የቀጠለ ሲሆን ሁለቱም ኦነግ-ሸኔ እና የመንግስት ኃይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል በሚል ተከሰዋል። እነዚህ ኩነቶች በመንግስት እና በኦነግ-ሸኔ መካከል ውጊያ ከሚደረግባቸው አካባቢዎች ጋር የተገናኙ ናቸው።
በዚህ ዘገባ ውስጥ የተካተቱ
- ከጥቅምት 22 እስከ ሕዳር 21, 2015 የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
- ወርሀዊ ትኩረት፡ በኦሮሚያ ክልል ግጭት ተባብሷል
ከጥቅምት 22 እስከ ሕዳር 21, 2015 የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
የሰላም ድርድሩ በትግራይ ክልል በመጀመሪያ ላይ ግጭት እንዲቆም አድርጓል። ከ10 ቀናት ድርድር በኋላ ጥቅምት 23 ቀን የኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ ለዘለቄታዊ ሰላም ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈራርመዋል። ይህ ስምምነት ተከትሎ በኬኒያ ናይሮቢ ለስድስት ቀናት ውይይት የተካሄደ ሲሆን በመቀጠልም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የትግራይ መከላከያ ሰራዊት (ቲዲኤፍ) በመባል የሚታወቁት የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች አዛዦች የከፍተኛ አዛዦች ለዘለቄታዊ ሰላም ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነትን ተግባራዊ የማድረግ መግለጫ ተፈራርመዋል (ሰለነዚህ ሰነዶች የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከጥቅምት 19-25, 2015 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከህዳር 3-9, 2015 ይመልከቱ)። ቀደም ሲል የወጡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ሁለቱም ወገኖች የተደረሱትን ስምምነቶች በመከተል ላይ ሲሆኑ የትህነግ/ህወሓት ባለስልጣናት የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች ከማይ ቅነጣል፣ ዛላምበሳ፣ ነበለት፣ ጨርጨር፣ ኩኩፍቶ፣ ሕጉምብርዳ ፣ በሪተኽላይ እና አበርገሌ ግንባሮች መልቀቃቸውን ሪፖርት አድርገዋል (ትህነግ/ህወሓት፣ ህዳር 22, 2015፤ አዲስ ስታንዳርድ፣ ህዳር 23, 2015)። የመንግስት ኃይሎች በተመሳሳይ እንደ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያሉ መሰረታዊ አገልግሎቶችን በክልሉ ወደ ነበሩበት ለመመልሰ ጥገና የጀመሩ ሲሆን በሽሬ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት “በጥቂት በቀናት ውስጥ” ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ ህዳር 22, 2015፤ ኢቢሲ፣ ህዳር 19 2015)።
የሰላም ስምምነቱ የውጭ ኃይሎች ከትግራይ ክልል ለቀው እንዲወጡ ቢገልፅም፣ የኤርትራ ኃይሎች ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰዎችን መግደላቸውእና በቁጥጥራቸው ስር “ባሉ በሰሜን እና ሰሜን ምዕራብ ትግራይ የሚገኙ ቢያንስ ደርዘን የሚሆኑ ከተሞች ውስጥ ከተኩስ አቁሙ በኃላ” ሱቆችን እና ተሽከርካሪዎችን መዝረፋቸው ተነግሯል (ሮይተርስ፣ ህዳር 23, 2015)።
በጋምቤላ ክልል ጥቅምት 30 ቀን ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሌ ብሔር ታጣቂዎች በአኝዋክ ዞን ዲማ ወረዳ ባንዴራ ቀበሌ ውስጥ በጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይል ላይ የደፈጣ ጥቃት ሰንዝረው የወረዳ ፖሊስ አዛዥን ጨምሮ ሁለት የክልሉ ፖሊስ አባላትን ገድለው አንድ ሌላ ፖሊስ አቁስለዋል። ከአንድ ቀን በፊት ታጣቂዎቹ የሰላማዊ ሰዎችን መኪና በማስቆም ሊያደርጉት የነበርው ጥቃት ከከሸፈ በኃላ የመንግስት ኃይሎች የታጠቀውን ቡድን በማፈላለግ ላይ ነበሩ።
በሶማሌ ክልል በሲቲ ዞን ደኸይሚድ ወረዳ እና ጃራር ዞን ደገሃመዶ ወረዳ ህዳር ጥቅምት 30 ቀን በሶማሌ እና በአፋር ብሔረሰብ ታጣቂዎች መካከል ውጊያዎች የተመዘገቡ ሲሆን 18 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። በዚህ አካባቢ በአፋር እና በሶማሌ ክልል መንግስታት መካከል የይገባኛል ውዝግብ ስላለ በአካባቢው ግጭት የተለመደ ነው (የዚህን ግጭት መነሻ ላይ የበለጠ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦ የአፋር–ሶማሌ ድንበር ግጭት ገፅን ይመልከቱ)።
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ላይ ህዳር 9 ቀን በቅርቡ በመንግስት የቀረበውን ‘ክላስተርን መሰረት ያደረገ አስተዳደራዊ መዋቅር’ በመቃወም ሃይል የተቀላቀለበት ተቃውሞ ተደርጉ ነበር። ለዚህ ምላሸ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ከህዳር 15 ጀምሮ የጉራጌ ዞን በፌዴራል ፖሊስና በክልሉ ልዩ ኃይል በሚመሩት በኮማንድ ፖስት ስር እንደሚተዳደር ገልፀዋል። እንደ አካባቢው ባለስልጣናት ከሆነ “የጉራጌ ዞን እንደ ክልል ዕውቅና እንዲሰጠው በቀረበው ጥያቄ ምክንያት የዞኑን የፀጥታ ጉዳዮች በመደበኛ ሂደት ለማስተዳደርና ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል” (ደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ኤጀንሲ፣ ህዳር 15, 2015)። ከኮማንድ ፖስቱ ምስራታ በኃላ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት አባልን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መታሰራቸው ተዘግቧል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ህዳር 14, 2015፤ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ ህዳር 22, 2015)።
በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት ከዚህ በታች ባለው ወርሀዊ ትኩረት ተሸፍኗል።
ወርሀዊ ትኩረት፡ በኦሮሚያ ክልል ግጭት ተባብሷል
የኢትዮጵያ ሰሜናዊ ግጭት ተፋላሚ ወገኖች የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ እየቀዘቀዘ ባለበት ወቅት በኦሮሚያ ያለው ግጭት በከፍተኛ ደረጃ እየተጠናከረ የመጣ ሲሆን ባለፈው ወር በክልሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ ብዛት ያላቸው የተደራጁ የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ተመዝግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ግራፍ ይመልከቱ)።
ትኩረት ወደ ኦሮሚያ እና በክልሉ ውስጥ ስላለው ዘርፈ ብዙ ግጭት ሲዞር ይህ ግጭት በሰሜን እንደነበረው አይነት ግጭት እና ይህ ግጭት ካደረሰው ጥፋትና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ጋር ተመሳሳይ ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል ወይ የሚለው ጥያቄ ይነሳል። በዚህ ወርሀዊ ትኩረት ከጥቅምት 22 እስከ ሕዳር 21, 2015 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ የታየውን የግጭት አዝማሚያ፣ ግጭቱ ከሰሜን ግጭት ጋር ተመጣጣኝ ደረጃ ላይ ሊደርስ የሚችልበትን አቅም እና የሚያስከትለውን መዘዝ እንተነትናለን።
ኦሮሚያ ከጥቅምት 22 እስከ ሕዳር 21, 2015 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ
ከጥቅምት 22 እስከ ሕዳር 21, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ አክሌድ በኦሮሚያ ክልል የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች መጨመራቸውን የዘገበ ሲሆን እነዚህ ግጭቶች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከፍ ብለዋል። በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ የኦነግ-ሸኔ ኃይሎች በምዕራብ ወለጋ ዞን መንዲ፣ በምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ እና በሰሜን ሸዋ ዞን ጉንዶ መስቀል ከተሞችን ጨምሮ በከተሞች ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ጥቃት ሰንዝረዋል (ከታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። በነቀምት ከተማ የኦነግ-ሸኔ ኃይሎች የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ካምፕን እና እስር ቤትን ለአጭር ጊዜ በመቆጣጠር እስረኞችን በመፍታት የጦር መሳሪያ ወስደዋል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ጥቅምት 30, 2015)። ብዙም ሳይቆይ የኦነግ-ሸኔ ኃይሎች የመንዲ ከተማን ከስድስት እስከ ሰባት ቀናት ያህል ተቆጣጥረው የቆዩ ሲሆን የመንግስት ኃይሎች በህዳር 1 ቀን እንደገና ከተማውን መቆጣጠር ችለዋል። በሰሜን ሸዋ ዞን ጉንዶ መስቀል ላይ የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች ገብተው ቤቶችን አቃጥለው እና ባንኮችን ዘርፈው ከተማውን ለቀው ወጥተዋል። ዘገባዎች እንዳመላከቱት በጥቅምት ወር የመጨረሻ ሳምንት እና በህዳር ወር በመጀመሪያው ሳምንት ውስጥ ታጣቂው ቡድን በምስራቅ ወለጋ ዞን ከሚገኙ 21 ወረዳዎች ውስጥ 11 ወረዳዎችን ተቆጣጥሯል (ኢትዮጵያ ሪፖርተር፣ ጥቅምት 24, 2015)። በህዳር አጋማሽ የመከላከያ ሠራዊት ከእነዚህ ወረዳዎች ውስጥ የተወሰኑትን መልሶ መቆጣጠር ችሏል (ኢ.ኤም.ኤስ፣ ህዳር 10, 2015)።
ከጥቅምት 22 እስከ ሕዳር 21, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ኦነግ-ሸኔ በምዕራብ ወለጋ ዞን “በጊምቢ ወረዳ የሚገኙ ወደ 32 የሚጠጉ ቀበሌዎችን” ጨምሮ በርካታ የገጠር ቦታዎችንም ተቆጣጥሯል (ኢትዮጵያ ሪፖርተር፣ ጥቅምት 24, 2015)። በምዕራብ ጉጂ ዞን በኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች እና በአካባቢው ታጣቂዎች መካከል ዳግም ጦርነት የተቀሰቀሰ ሲሆን ኦነግ-ሸኔ በጉጂ ዞን ሊበን፣ ጂዶላ፣ ዋዴራ እና ሌሎች ቀበሌዎችን ተቆጣጥሯል። የኦነግ-ሸኔ ተጽእኖ እየጨመረ በሄደ ቁጥር እና የፀጥታ ኃይሎች በየአካባቢው ብዙም ባለመኖራቸው ምክንያት በየአካባቢው የሚነሱ የእርስ በእርስ ግጭቶች ተባብሰዋል። ባለፈው ወር በምስራቅ ወለጋ እና በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች ሰሜናዊ አካባቢዎች በአማራ ብሔር ታጣቂዎች እና ከእነሱ ጋር የሚተባባሩት የፋኖ ታጣቂዎች ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ጋር በመዋጋታቸው በአካባቢው ግጭት ተባብሷል። ባለፈው አንድ አመት የአማራ ብሔር ታጣቂዎች የተሳተፉበት ግጭቶች በእነዚህ የኦሮሚያ አካባቢዎች በከፍተኛ ደረጃ ተባብሶ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረስ ሲሆን የተፈናቀሉ ሰላማዊ የኦሮሞ እና የአማራ ተወላጆች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ዘግቧል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ህዳር 15, 2015፤ ቪኦኤ አማርኛ፣ ህዳር 14, 2015)።
የኦሮሚያ ግጭት፡ ከዚህ በላይ ሊባባስ ይቻላል?
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት እና በትህነግ/ህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት እስካሁን ያሳየው የመጀመሪያ ስኬት የፌዴራል መንግስት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ኦሮሚያ ግንባር ሊያሸጋግረው የሚችልው ከፍተኛ የፀጥታ ኃይል ሊኖረው እንደሚችል ይጠቁማል። በሚቀጥሉት ወራት በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ወታደሮች እና ከባድ መሳሪያዎች ወደ ኦሮሚያ ሊላኩ የሚችሉ ቢሆንም ይህ አዲስ አደራጃጀት ምን ያህል ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ግን ግልፅ አይደለም። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባለፉት ጥቂት ወራት በትግራይ ክልል በትህነግ/ህወሓት ላይ አዲስ እና የታደስ የጦርነት ስልት ቢያሳይም የአማፂ አይነት ውጊያ ሲያጋጥመው ግን ተግዳሮቶች አጋጥመውታል። ይህ የታየው በ2013/2014 የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የትግራይ ክልልን ለመቆጣጠር ባደረገው ጦርነት እና በመቀጠልም በትህነግ/ህወሓት ኃይሎች ተሸንፎ ቦታዎችን በለቀቀበት ወቅት ነው (ኒውዮርክ ታይምስ፣ ግንቦት 25, 2013)። በኢትዮጵያ ፀረ-ሽምቅ ኃይሎችን እንዲከላከሉ የተቋቋሙት የክልል ልዩ ኃይሎች ቢሆኑም የኦነግ-ሸኔን ግስጋሴ ለማስቆም ግን ውጤታማ ያልሆኑ ይመስላሉ።
የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች አዳዲስ ቦታ ለመያዝ በሚንቀሳቀሱብት ወቅት እና የመንግስት ኃይሎች ታጣቂዎችን በአዳዲስ መሳሪያዎች ታግዘው ለማጥፋት በሚያደርጉት ጥረት ምክንያት በኦሮሚያ ውስጥ ያለው ጦርነት የበለጠ ተባብሶ የሚቀጥልበት ሁኔታ ከፍ ያለ ነው። ይህ ቀደም ሲል በቡድኑ ላይ መንግስት በሰው አልባ አውሮፕላን የታገዘ የአየር ድብደባ በሚያደርግበት ወቅት የታየ ሲሆን የአየር ጥቃቱ እና ከጥቃቱ ጋር ተያያዥነት ያለው የሟቾች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል (መንግስት በኦነግ–ሸኔ ላይ የሚያደርገው የአየር ድብደባ ላይ የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ወርሀዊ: ከመስከረም 21 እስከ ጥቅምት 21, 2015ን ይመልከቱ)። የእነዚህ እርምጃዎች ውጤታማነት አከራካሪ ነው። በአንድ በኩል ልክ እንደ ትግራይ ክልል የአየር ድብደባው ታጣቂዎች በቡድን መሰባሰብ እንዳይችሉ የበለጠ አዳጋች በማድረግ ኦነግ-ሸኔ የጭነት መኪናዎችን (ኮንቮይዎችን) እንዳይጠቀም አድርጓል። አንዳንድ የሰው አልባ አውሮፕላን ጦርነት ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ግጭት የሰው አልባ አውሮፕላኖች “የጨዋታ ለውጥ እያደረጉ መሆናቸውን” ጠቁመዋል (ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ታህሳስ 11, 2015)። በሌላ በኩል ባለፉት ሁለት ወራት የተጠናከረ የአየር ጥቃት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን ይህም ለፀረ-መንግስት ኃይሎች ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያገኙ አድርጓል።
በኦሮሚያ ያለው ግጭት ውስብስብ ነው፤ ልክ ከአማራ ክልል የመጡ ታጣቂዎች አይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለያዩ ወገኖች በግጭቱ ተሳትፎአቸውን እያጠናከሩ በሄዱ ቁጥር ግጭቱ እየተባባሰ ሄዶ ከአካባቢው ሁኔታ እየሰፋ ሄዷል። ኦነግ-ሸኔ ብዙ ቦታዎችን እየተቆጣጠረ በሄደ ቁጥር በክልሉ ያለው የፀጥታ እጦት እንደ በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ያሉ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች በሚኖሩበት ስፍራ የእርስ በእርስ ግጭቶች እንዲቀጣጠሉ አድርጓል። በምስራቅ ወለጋ ዞን በ1960ዎቹ እና 1970ዎቹ በአማራ እና ኦሮሞ ክልል ድንበር በስተደቡብ በሚገኙ መንደሮች ውስጥ የሰፈሩ የአማራ ተወላጆች በመሬት እና በንብረት ላይ አልፎ አልፎ ከኦሮሞ ተወላጆች ጋር ይጋጩ ነበር (ተፈራ፣ እ.ኤ.አ. 2017)። እነዚህ ግጭቶች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስልጣን ከያዙ በኋላ በከፍተኛ ሁኔታ የተባባሱ ሲሆን በኦሮሞ እና በአማራ ብሄር ታጣቂዎች መካከል የተገደቡ ግን መደበኛ ግጭቶች ይከሰታሉ፣ ይህም ግጭት ብዙ ጊዜ ሰላማዊ ሰዎችን በማፈናቀል የታጀበ ነው (ቪኦኤ፣ ህዳር 14, 2015)። እነዚህ በእርሻ መሬት እና በሀብት ምክንያት የሚነሱ የአካባቢ ግጭቶች እየተጠናከሩ በሄዱ ቁጥር ሌሎች አካላት እንዲሳተፉ አድርጓል። በኦሮሚያ የሚገኙ አማራዎች ከእርሻ መሬቶቻቸው በግዳጅ መፈናቀላቸው የአማራ ታጣቂዎች – አንዳንድ ጊዜ ከአማራ ክልል የመጡ ፋኖ በመባል የሚጠሩት – እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል (ኩሬት ኦሮሚያ፣ ጥቅምት 7, 2015)።
በዚህ አካባቢ ከተከሰቱት በጣም ኃይለኛ ጥቃቶች መካከል አንዳንዶቹ የተመዘገቡት ከጥቅምት 22 እስከ ሕዳር 21, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። ህዳር 20 ቀን የአማራ ብሔር ታጣቂዎች እንደሆኑ የሚገመቱ የአማራ ኃይሎች ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ጋር በኪረሙ የተዋጉ ሲሆን 10 የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት እና የኪረሙ ወረዳ ፍርድ ቤት ዳኛ እንደሆኑ የተገለፀ የአካባቢው አስተዳደር ባለስልጣንን ጨምሮ 11 ሰዎችን ገድለዋል። አንድ ቀን ቀደም ብሎ በኪረሙ ወረዳ በተፈጠረ አለመረጋጋት ምክንያት በአንድ ትምህርት ቤት ተጠልለው የነበሩ ከ100 በላይ ሰዎችን ማንነቱ ያልታወቀ የታጣቂ ቡድን ተኩሶ መግደሉ ተዘግቧል። ቀደም ሲል ህዳር 9 ቀን የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል የአማራ ተወላጅ እስረኞች ከምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ወደ ነቀምት ከተማ ለፍርድ ሂደት ሲያጓጉዙ በፋኖ ታጣቂዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል። በዚህም ለአራት ቀናት የዘለቀ ከፍተኛ ግጭት በመፈጠሩ የአማራ ተወላጆችን ጨምሮ በርካቶች ለሞት ተዳርገዋል (ሰለ እነዚህ ክስተቶች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከህዳር 10-16, 2015 ይመልከቱ)። የኪረሙ ክስተት ከመፈጠሩ ከጥቂት ቀናት በፊት ከኪረሙ ወረዳ በስተምስራቅ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርቴ ጃርዴጋ ወረዳ አሊቦ ከተማ የፋኖ ታጣቂዎች በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ያደረሱት ጥቃት በሰፊው ተዘግቧል (ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ፣ ህዳር 10, 2015)። ኦነግ-ሸኔ ከዚህ ቀደም ለተከሰቱት ተመሳሳይ ድርጊቶች ምላሽ የሰጠ ሲሆን የፋኖ ታጣቂዎችን ጨምሮ ከአማራ ታጣቂዎች ጋር ባለው ውጊያ መሳተፉን አረጋግጦ “ከዚህ ቀደም አሰቃቂ ግድያ የፈፀሙ እና ብሔር ተኮር ግጭት ለማነሳሳት የሞከሩትን የአማራ ክልል ታጣቂዎች መልሷል” ሲል ገልጿል (ኢትዮጵያ ኢንሳይት፣ ግንቦት 24, 2014)።
በመላው ምዕራብ ኦሮሚያ በገጠርም በከተማም በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ይገኛሉ። በኦሮሚያ ያለው ግጭት እየተባባሰ በሄደ ቁጥር በእነዚህ ማህበረሰቦች ላይ የሚደርሰው ብሔር ተኮር ግጭት እየጨመረ መምጣቱ አይቀርም።
በኦሮሚያ ክልል እየጨመረ የመጣው ጦርነት መዘዙ
በኦሮሚያ ክልል ጦርነቱ ይበልጥ እየተጠናከረ ከመጣ በተቀረው የሀገሪቱ ክፍል ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከፍተኛ ቀውስ ሊፈጥር ይችላል። በሰሜን እና ከአገሪቱ ዋና ከተማ ርቆ የሚገኘው ከትግራይ ክልል በተቃራኒ ኦሮሚያ በሃገሪቱ መሃል ላይ የሚገኝ ሲሆን ዋና ከተማዋን አዲስ አበባን እና ዘጠኝ ክልሎችን እና ድሬዳዋ ከተማን ያዋስናል። በትግራይ እና በምዕራብ ኦሮሚያ ላለፉት ሁለት አመታት የኮሙዩኒኬሽን ማቋረጥ ሁለቱም ግጭቶች የተካሄዱት የመረጃ እጥረት ባለበት አካባቢ ነው። ከእነዚህ አካባቢዎች ውጪ ያሉ ነዋሪዎች በሰው በሰው ግንኙነት ካላደረጉ በስተቀር ስለግጭቶቹ መረጃ ለማግኘት ይቸገራሉ።
አሁን ያለው ግጭት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ እና ደቡብ ጫፍ ላይ ያተኮረ ነው። ነገር ግን ጦርነቱ ወደ መካከለኛው እና ምስራቃዊው የክልሉ ክፍሎች (ለምሳሌ አርሲ እና ሀረርጌ ዞኖች) ቢስፋፋ የፀጥታ ችግሩ እና ተያያዥ ኢኮኖሚያዊ መዘዞቹ የከፋ ሊሆኑ ይችላል። በውጊያዎች እና ኦነግ-ሸኔ በተደጋጋሚ ሰላማዊ ሰዎችን በማፈኑ ምክንያት በሰሜን ሸዋ ዞን ወደ አማራ ክልል እና በአዳማ-መተሃራ በኩል ወደ ጅቡቲ የሚወስዱት የትራንስፖርት መስመሮች በመጠኑ አስቸጋሪ ሆነዋል (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ የካቲት 2, 2014)። ይህም በሀገር ውስጥ ሸቀጦችን ማጓጓዝ እና በጅቡቲ ወደብ በሚገቡ እቃዎች ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል። በዚህም ምክንያት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመሰረታዊ የምግብ ፍጆታ ላይ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል። ለምሳሌ በጥቅምት ወር ኦነግ-ሸኔ ከቤንሻንጉል/ጉሙዝ ከአሶሳ ዞን በነቀምት ከተማ አድርጎ ወደ አዲስ አበባ የሚያገናኘውን ዋና መንገድ ዘግቷል። ቡድኑ ወደ አሶሳ የሚሄዱ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ አሽከርካሪዎችን አፍኖ መውሰዱንም ተነግሯል። በዋናው መንገድ በመዘጋት ምክንያት የከባድ መኪና እና የአውቶብስ ሹፌሮችን ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎች ለበርካታ ሳምንታት በጊምቢ ከተማ ለመቆየት ተገደው እንደነበር የአይን እማኞች ገልጸዋል። በመሆኑም መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች አሶሳ ዞን ውስጥ መግባት ባለመቻላቸው በአካባቢው የዋጋ ጭማሪ አስከትሏል (ዲደብሊው አማርኛ፣ 30 ጥቅምት, 2015)። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤንኦሲኤችኤ) ሪፖርቶች እንዳረጋገጡት “ከጥቅምት 21 ጀምሮ በኦሮሚያ በኩል የአሶሳ – አዲስ ዋናው መንገድ ዝግ በመሆኑ የሰብአዊ እና የንግድ አቅርቦቶችን ማንቀሳቀስ አልተቻለም” (ዩኤንኦሲኤችኤ፣ ህዳር 8, 2015)።
ሆኖም የአቅም ልዩነት እንዳለ ማወቅ አስፈላጊ ነው። ባለፉት ሁለት አመታት ትህነግ/ህወሓት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን ፊት ለፊት እንደተዋጋው ኦነግ-ሸኔ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን ፊት ለፊት ለመዋጋት አቅሙም ሆነ ወታደራዊ መሳሪያ የለውም። በተጨማሪም ኦነግ-ሸኔ በህዝቡ መካከል የተወሰነ ድጋፍ ሊያገኝ ቢችልም ትህነግ/ህወሓት ለ27 አመታት በስልጣን ላይ በቆየበት ጊዜ የሰበሰበው አይነት የውስጥ እና አለም አቀፍ የፖለቲካ ግብአት የለውም። ኦነግ-ሼኔ እና ትህነግ/ህወሓት በዋናነት አባል የሆኑበት የኢትዮጵያ ፌደራሊስት እና ኮንፌደራሊስት አንድነት ኃይሎች ግንባር በጥቅምት 2014 ከተመሰረተ በኃላ ምንም አይነት የጋራ ዘመቻ አልተካሄደ ሲሆን ትህነግ/ህወሓት በአማራ ክልል ከኦሮሚያ ልዩ ዞን በዚሁ አመት ላይ (2014) ባፈገፈገበት ወቅት የሁለቱ ኃይሎች ግንኙነት የቀረ ይመስላል። ስለዚህ ኦነግ-ሸኔ በሰሜናዊው ክፍል በታየው መጠን ግጭት ውስጥ የመሳተፍ እድሉ በጣም ዝቅተኛ ነው።
የኦነግ-ሸኔ አመራር በሰላም ውይይት ለመሳተፍ ምንም አይነት ተነሳሽነት ያለው አይመስልም። ኦነግ-ሸኔ በቅርቡ በሰጠው መግለጫ ለግጭቱ መባባስ መንግስትን ተጠያቂ በማድረግ በመንግስት ተልከዋል የተባሉትን የባህል መሪዎች የሽምግልና ጥረት ውድቅ አድርጓል (ትዊተር @ኦዳተርቢደብሊውቢኦ፣ ህዳር 20, 2015)። በተመሳሳይ ቡድኑ እንድ የፖለቲካ ተወካይ እና ወታደራዊ እዝ መዋቅር እንደሌለው በመግለፅ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ከኦነግ-ሸኔ ጋር ለመደራደር ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ገልፀዋል (ኢቢሲ፣ ህዳር 21, 2015)።
የመንግስት እና የኦነግ-ሸኔ ሃይሎች በቅንነት ወደ ድርድር ካልገቡ በኦሮሚያ ያለው ግጭት መቀጠሉ የማይቀር ነው። አሁን ካለው ሁኔታ አንፃር በተለይ በኦሮሚያ ክልል ሰሜናዊ ምዕራብ አካባቢዎች ግጭት በተከሰተባቸው ዞኖች ውስጥ የሚኖሩ የሰላማዊ ሰዎች ሁኔታ ተባብሶ ሊቀጥል ይችላል።