የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግስት ኃይሎች መካከል ያለው ውጊያ የቀጠለ ሲሆን በተጨማሪም የእጅ ቦምብ ጥቃቶች ደርሰዋል። በትግራይ ክልል የተቃውሞ ሰልፍ የቀጠለ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል ውጊያዎች እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ተከስተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በሶማሊያና በኢትዮጵያ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ተፈጥሯል።
በአማራ ክልል የቀጠለው ጦርነት
በአማራ ክልል በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ በሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ጎንደር፣ ደቡብ ወሎ፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ዋግ ኽምራ እና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች መካሄዱ ተዘግቧል። በክልሉ ውጊያው እየቀጠለ ቢሆንም ከየካቲት ወር ጀምሮ ውጊያው በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰ ይመስላል። ባለፈው ሳምንት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈፃፀም ለመከታተል የተቋቋመው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት በየካቲት ወር መጨረሻ በፀጥታ ስጋት ምክንያት ተዘግቶ የነበረውን ደብረ ብርሃን፣ ሸዋ ሮቢት እና ደሴ ከተሞችን የሚያገናኘውን መንገድ መከፈቱን አስታውቋል።1ቪኦኤ አማርኛ፣ ‘የደብረ ብርሃን-ደሴ መንገድ ከወር በኋላ ሲከፈት ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጥ ተጠየቀ፣’ መጋቢት 30, 2016
መጋቢት 26 ቀን በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም ከተማ ከፋኖ ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ የተጠረጠረ ተማሪ በሚማርበት የመሰናዶ ትምህርት ቤት የእጅ ቦምብ በመወርወር በትንሹ 27 ተማሪዎችን አቁስሏል። ይህን ድርጊት ተከትሎ በእለቱ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች የቆሰሉ ተማሪዎችን ወደ ሆስፒታል ሲያጓጉዝ የነበረ መኪናን አስቁመው የተጎዱትን ተማሪዎች በመንገድ ዳር ጥለው፣ ሾፌሩን እስከነመኪናው አፍነው ወስደዋል።2ዓለምነው መኮንን፣ ሸዋዬ ለገሠ እና እሸቴ በቀለ፣ ‘በፍኖተ ሰላም በተከሰተ ፍንዳታ 34 ሰዎች መቁሰላቸውን የምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ ገለጹ፣’ ዲደብሊው አማርኛ፣ መጋቢት 30, 2016 መጋቢት 28 ቀን ሌላ የእጅ ቦምብ በፍኖተ ሰላም ከተማ እህል ገብያ ላይ ማንነቱ ባልታወቀ ሰው የተወረወረ ሲሆን በትንሹ 27 ሰላማዊ ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ጉዳት ከደረሰባቸው አብዛኛዎቹ ሴቶች ናቸው።3ዓለምነው መኮንን፣ ሸዋዬ ለገሠ እና እሸቴ በቀለ፣ ‘በፍኖተ ሰላም በተከሰተ ፍንዳታ 34 ሰዎች መቁሰላቸውን የምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ ገለጹ፣’ ዲደብሊው አማርኛ፣ መጋቢት 30, 2016 የአማራ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጥቃቱን የፈፀመው “ፅንፈኛ ቡድን” ነው ሲል ከሷል።4የአማራ ኮሙዩኒኬሽን፣ ‘ጽንፈኛዉ ቡድን ዛሬም በፍኖተሰላም ከተማ ገበያ ላይ በተሰበሰበ ህዝብ መሀል የሽብር ተግባር ፈጽሟል፣’ መጋቢት 28, 2016 በአማራ ክልል ከተሞች የእጅ ቦምብ ጥቃቶች የሚስተዋሉ ሲሆን ባለፈው አንድ ዓመት 13 ጥቃቶች ደርሰዋል።
ስልፎች በትግራይ ክልል
መጋቢት 27 ቀን በመቶዎች የሚቆጠሩ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በትግራይ ርዕሰ መዲና መቀሌ የተራዘመውን የምረቃ ቀን በመቃወም ስልፍ አድርገዋል። የትግራይ ክልል ፖሊስ ስልፈኞችን ለመበተን በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ጥቃት በማድረስ፣ አየር ላይ ጥይት በመተኮስ 10 ተማሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል። ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ተቃዋሚ ስልፈኞች ቆስለዋል። ሰልፈኞቹ ለክልሉ መንግስት ስለሰልፉ ቀድመው ባለማሳወቃቸው ሰልፉን መበተኑን ፖሊስ አስታውቋል።5ሚሊዮን ኃይለሥላሴ፣ ነጋሽ መሐመድ እና እሸቴ በቀለ፣ ‘መቀሌ ዉስጥ ሰልፍ የወጡ ተማሪዎች ተደበደቡ፣’ ዲደብሊው አማርኛ፣ መጋቢት 27, 2016
በሌላ በኩል መጋቢት 22 ቀን በደቡብ ትግራይ ዞን ኮረም ከተማ የአማራ ተወላጆች ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን በትግራይ እና በአማራ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች በአማራ እና በትግራይ ታጣቂዎች መካከል የተፈጠረውን ውጊያ እንዲፈታ የፌዴራል መንግስትን ጠይቀዋል። በየካቲት ወር በድንበር አካባቢ ውጊያ የተቀሰቀሰ ሲሆን ይህ ውጊያ በመጋቢት ወርም በመቀጠሉ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ስጋት ላይ ይጥለዋል። መጋቢት 26 ቀን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የትግራይ ክልልን “የሰላም ስምምነቱ የሚፃረሩ ተግባራትን” እያደረገ ነው ሲል የከሰሰ ሲሆን የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎችን እጣ ፈንታ በህዝበ ውሳኔ ብቻ ለመፍታት ያለውን ፍላጎት በድጋሚ አጽንኦት ሰጥቷል።6የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ‘የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ፣’ መጋቢት 26, 2016 የደቡብ ትግራይ ዞን አስተዳደር በበኩሉ ይህንን ውንጀላ ውድቅ በማድረግ በቅርቡ በዞኑ ለተፈጠረው ግጭት የአማራ ኃይሎችን ተጠያቂ ማድረጉን ቀጥሏል።7ቪኦኤ አማርኛ፣ ‘የትግራይ እና የአማራ ክልሎች ችግሮችን በውይይት ብቻ እንዲፈቱ መንግሥት አሳሰበ፣’ መጋቢት 26, 2016
ግጭት በኦሮሚያ ክልል
በኦሮሚያ ክልል በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ) — በመንግሥት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ተብሎ የሚጠራው — እና በመንግስት ኃይሎች መካከል የሚደረገው ውጊያ የቀጠለ ሲሆን ባለፈው ሳምንት በምዕራብ ወለጋ እና ጉጂ ዞኖች ውጊያ መደረጋቸው ተዘግቧል። በሌላ በኩል በምዕራብ ወለጋ ዞን በቆንዳላ ወረዳ የተደረገ ውጊያን ተከትሎ የመንግስት ኃይሎች ኦነሠ/ኦነግ–ሸኔን ይደግፋል ብለው የከሰሱትን ሰላማዊ ሰው ተኩሰው መግደላቸው ተነግሯል። መጋቢት 26 ቀን በምዕራብ ሸዋ ዞን በአመዩ ወረዳ የኦነሠ/ኦነግ–ሸኔ ታጣቂዎች በርካታ የአማራ ተወላጆችን መግደላቸው ተዘግቧል።8ኤክስ @ኤኤኤ_አማራ፣ መጋቢት 27, 2016 በሌላ በኩል መጋቢት 26 ቀን በክልሉ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ቶሌ ወረዳ በመንግስት ታጣቂዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘረ ጥቃት 20 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ ግድያውን አውግዞ መንግስት ባልታጠቁ ሰዎች ላይ የኃይል እርምጃ እየወሰደ ነው ሲል ከሷል።9የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ ‘መንግስት በኃይል የተቆጣጠረውን የፖለቲካ ስልጣን ለመጠበቅ በብልጽግና ፓርቲ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈፀሙ የጦር ወንጀሎች፣’ መጋቢት 27, 2016
የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነት
በታህሳስ ወር ላይ በኢትዮጵያ እና በሶማሌላንድ — እውቅና ያልተሰጠው ራስ ገዝ አስተዳደር — መካከል የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል ያለው ውዝግብ መጋቢት 26 ቀን ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ሶማሊያ የኢትዮጵያን አምባሳደር እንደምታባርር እና የራሷን አምባሳደር ከአዲስ አበባ እንደጠራች አስታውቃለች።10ፈላስቲን ኢማን እና መሃመድ ኦላድ ሀሰን፣ ‘ሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደርን አባረረች፣ ሁለት ቆንስላ ፅህፈት ቤት እንዲዘጋ አዘዘች፣’ የአሜሪካ ድምጽ፣ መጋቢት 26, 2016 በሶማሊያ ከሚገኙት የፌዴራል ግዛቶች አንዷ የሆነችው የፑንትላንድ ባለስልጣናት ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር “በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በኢነርጂ ትብብር እና በጋራ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች” ላይ ባለፈው ሳምንት ከተወያዩ በኋላ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል ያለው የሻከረ ግንኙነት ተካሯል።11የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ ‘ኢትዮጵያ እና ፑንትላድ ያላቸውን የተለያዮ ግንኙነቶች ለማጠናከር ተስማሙ፣’ መጋቢት 25, 2016 የሶማሊያ ሕገ-መንግስት ላይ አዲስ ለውጥ መደረጉን ተከትሎ የፑንትላንድ መንግስት የሶማሊያ ፌዴራል መንግስትን ስልጣን እንደማይቀነል ከገለፀ በኋላ በፑንትላንድ እና በሶማሊያ ፌዴራል መንግስት መካከል ያለው ግንኙነት ሻክሯል።12ሮይተርስ፣ ‘የሶማሊያ ፑንትላንድ አጨቃጫቂ የሕገ መንግሥት ለውጦች በኋላ ለፌዴራል መንግሥት እውቅና አልሰጥም አለች፣’ መጋቢት 22, 2016
ኢትዮጵያ በጨረፍታ
መጋቢት 21–27, 2016
ይህ መረጃ/ዳታ ከመጋቢት 21 እስከ 27, 2016 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
የኩነት አይነቶች
ውጊያዎች: 16 ኩነቶች
ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 2 ኩነቶች
ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 9 ኩነቶች
የአመፅ ግጭት: 0 ኩነት
ሰልፎች: 1 ኩነት
ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 0 ኩነት