የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በበትግራይ ክልል የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳብቸው በደቡብ ትግራይ ዞን በሚገኙ አካባቢዎች በአማራ እና በትግራይ ክልል ታጣቂዎች መካከል ውጊያ የተሰፋፋ ሲሆን በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በመንግስት ኃይል እና በአማፂያን መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች ቀጥለዋል።
በትግራይ የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች የተሰፋፋው ውጊያ
ከአማራ እና ከትግራይ ክልል በመጡ ታጣቂ ኃይሎች መካከል በደቡብ ትግራይ ዞን በራያ አላማጣ፣ ዛታ፣ ኦፍላ እና አላማጣ ወረዳዎች የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች በተዘገቡ ውጊያዎች ምክንያት ውጥረት ጨምሯል። ውጊያው ሚያዚያ 5 ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 7 ድረስ የዘለቀ ሲሆን የፌዴራል ኃይሎች ጣልቃ ገብተው አላማጣ ከተማን ሲቆጣጠሩ ውጊያው አቁሟል። የሰሜን ወሎ እና የዋግ ኽምራ ዞኖች ባለስልጣናት እንደገለፁት ከሆነ ዳግም በተቀሰቀሰው ግጭት የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ50,000 በላይ ደርሷል።1የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ፣ ‘ኢትዮጵያ፡ ወቅታዊ መረጃ ቁጥር 2፡ ተፈናቃዮች በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ እና ዋግ ኽምራ ዞኖች (ሚያዚያ 14, 2016)፣’ ሚያዚያ 14, 2016
የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ጥቅምት 2015 ካበቃ በኋላ በደቡብ ትግራይ ዞን — በይፈ የትግራይ ክልል አካል የሆነ ነገር ግን በአማራ ክልል ባለስልጣናት የሚተዳደር — ውጊያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተው በየካቲት ወር ነበር። ውጊያው በመጋቢት ወርም ወጥሏል። የባለፈው ሳምንት ግጭት በአካባቢ ሽፋን ሆነ በቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ውጊያው እየጨመረ እንደመጣ የሚያሳይ ሲሆን በፕሪቶሪያ ስምምነት የተገኘውን ሰላም አደጋ ላይ ይጥላል።
የትግራይ ጊዜያዊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ውጊያው “የፕሪቶሪያ ስምምነት ከባድ ጠላቶች ሥራ” መሆኑን በመግለጫቸው አመልክተዋል።2ኤክስ@ረዳ_ጌታቸው፣ ሚያዚያ 7, 2016 የአማራ ክልላዊ መንግስት መግለጫ ያወጣ ሲሆን የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባርን የማንነት ጥያቄዎች በሚነሳባቸው ማለትም የአማራ ክልል የይገባኛል ጥያቄ በሚያናሳባቸው ምዕራብ እና የደቡብ ትግራይ ዞኖችን በመውረር እና ጦርነት እንዲቀሰቅስ አድርጓል ሲል ከሷል።3የአማራ ክልል ፕሬዝደንት ቢሮ፣ ‘ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሰጠ መግለጫ፣’ ሚያዚያ 9, 2016 የፌዴራል ባለስልጣናት በውጊያው ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን ሁሉም ወገኖች የፕሪቶሪያን ስምምነት እንዲያከብሩ የጠየቁ ሲሆን የይገባኛ ጥያቄ የሚነሳባቸውን አካባቢዎችን ጉዳይ በሪፈረንደም ለመፍታት ያላቸውን ቁርጠኝነት ዳግም አመላክተዋል።4ቪኦኤ አማርኛ፣ ‘በራያ አላማጣ አካባቢ ግጭት የፌደራል መንግሥት ማሳሰቢያ ሰጠ፣’ ሚያዚያ 11, 2016፤ ቢቢሲ አማርኛ፣ ‘በአማራ እና ትግራይ አወዛጋቢ ቦታዎች ያለው አስተዳደር እንዲፈርስ ይደረጋል – የመከላከያ ሚኒስትሩ፣’ መጋቢት 14, 2016 በእነዚህ አካባቢዎች ውጊያዎች በስፋት ሊቀጥሉ የሚችል ሲሆን በሚቀጥሉት ሳምንታት ሰፊ ግጭት፣ ሰልፍ እና ብጥብጥ ሊያስከትሉ ይችላል።
በአማራ የቀጠለው ውጊያ
በአማራ ክልል በመንግስት ታጣቂዎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ እንደነበርም ተዘግቧል። በምዕራብ ጎጃም፣ በማዕከላዊ ጎንደር፣ በደቡብ ጎንደር፣ በሰሜን ሸዋ እና በአዊ ዞኖች የፋኖ ታጣቂዎች እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወታደሮች መካከል ውጊያ መፈጠሩ ተነግሯል። በምዕራብ ጎጃም ዞን ፈረስ ቤት — ከህዳር ወር ጀምሮ በተደጋጋሚ ግጭት በሚፈጠርበት አካባቢ — በነበረ ውጊያ የመንግስት ኃይሎች 64 የፋኖ ተዋጊዎችን መግደላቸውን እና በርካቶችን ማቁሰላቸውን አስታውቀዋል።5አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ‘ፈረስ ቤትን ለመቆጣጠር የመጣው የጽንፈኛ ኃይል መመታቱን የጎጃም ኮማንድፖስት አስታወቀ፣’ ሚያዚያ 7, 2016 በአዊ ዞን በነበረ ውጊያ ወቅት በመንግስት ወታደሮች የተተኮሰው ከባድ መሳሪያ በትንሹ አምስት ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።
ውጊያ እና የትራንስፖርት ገደብ በኦሮሚያ
በኦሮሚያ ክልል የሚደረጉ ውጊያዎች ቀጥለዋል። በምስራቅ ሸዋ ዞን በባቱ (ዝዋይ) ከተማ እና አካባቢዋ እንዲሁም በምስራቅ ወለጋ እና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ) — በመንግሥት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ተብሎ የሚጠራው — እና በመንግስት ኃይሎች መካከል ውጊያ ተደርጓል። ከሳምንት በፊት አንድ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ፖለቲከኛ በተገደሉበት በመቂ ከተማና አካባቢው በትራንስፖርት ሹፌሮች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈፀሙ ታውቋል። የፖለቲከኛውን ግድያ ተከትሎ የታወጀ የትራንስፖርት እንቅሰቃሴ ገደብን ለማስከበር የኦነሠ/ኦነግ–ሸኔ ኃይሎች ቢያንስ አንድ ሹፌር ሲገድሉ አራት የነዳጅ ማደያ ሠራተኞች አግተው የወሰዱ ሲሆን አንድ የጭነት መኪና እና በርካታ ባጃጆች አቃጥለዋል።6ገልሞ ዳዊት፣ ‘የበቴ ዑርጌሳን ግድያ ተከትሎ በባቱ እና መቂ ከተሞች በተቀሰቀሰ ግጭት ውጥረት መስፈኑ ተገለጸ፣’ ቪኦኤ አማርኛ፣ ሚያዚያ 9, 2016
ኢትዮጵያ በጨረፍታ
ሚያዚያ 5-11 2016
ይህ መረጃ/ዳታ ከሚያዚያ 5 እሰከ 11, 2016 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
የኩነት አይነቶች
ውጊያዎች: 33 ኩነቶች
ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 0 ኩነት
ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 13 ኩነቶች
የአመፅ ግጭት: 0 ኩነት
ሰልፎች: 2 ኩነት
ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 0 ኩነት