የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች አፈና እና ውጊያ መፈጸሙ የተገለጸ ሲሆን በአማራ ክልል በኦሮሚያ ልዩ ዞን አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ተገድለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በትግራይ ክልል የተፈናቀሉ ሰዎች የይገባኛል ጥያቄ ወደሚነሳባቸው አካባቢዎች መመለሳቸውን ቀጥለዋል። በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ቀጥሏል።
በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች አፈና እና ግድያ
ሰኔ 25 ቀን ከአማራ ክልል ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ወደ ዋና ከተማ አዲስ አበባ የሚወስደው A3 አውራ ጎዳና ላይ በመጓዝ ላይ የነበሩ 100 የዩንቨርስቲ ተማሪዎች የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ) — በመንግስት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሸኔ እየተባለ የሚጠራው — አባል እንደሆኑ በተጠረጠሩ ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገብረ ጉራቻ ከተማ አቅራቢያ ታግተዋል። ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስ እና ቀበሌ ታጣቂዎች ጋር በመሆን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ታግተው የተወሰዱትን ተማሪዎች ለማስለቀቅ ባደረገው ሙከራ ከታጣቂዎቹ ጋር የተዋጋ ሲሆን በዚህም የተወሰኑ ተማሪዎች ማምለጥ ችለዋል።
የዩኤስ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ከጥቂት ቀናት በኋላ በሰጡት መግለጫ ጥቃቱን እና ሌሎች የአፈና ድርጊቶችን አውግዘዋል።1ሮይተርስ፣ ‘በኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት ከ100 በላይ ሰዎች ለገንዘብ ታግተዋል ሲል የአሜሪካ ልዑክ ገለጸ፣’ ሐምሌ 1, 2016 ባለፈው አንድ አመት ውስጥ በኦሮሚያ ክልል በማህበረሰብ መሪዎች እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ አፈና እና ጥቃት አሳሳቢ እየሆነ የመጣ ሲሆን (ለተጨማሪ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ፡ ጥቅምት 3-9, 2016 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ፡ ጥቅምት 10-16, 2016 ይመልከቱ)2ፍሬድ ሃርተር፣ ‘ይህ ወረርሽኝ ነው’፡ የኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል የአፈና ስጋት፣’ ዘ ጋርዲያን፣ ጥር 14, 2016 እነዚህ ክስተቶች በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች አዋሳኝ በሚገኘው በሰሜን ሸዋ ዞን (ኦሮሚያ ክልል) የተለመዱ ናቸው። ሰኔ 2015, ከአማራ ክልል የመጡ በርካታ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በመታፈናቸው በአማራ ክልል የተቃውሞ ሰልፎ ተቀስቅሰው ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራ ክልል ኦሮሚያ ልዩ ዞን ኦነሠ/ኦነግ–ሸኔ እንደሆኑ የተጠረጠሩ ኃይሎች በከሚሴ ከተማ የኦሮሚያ ልዩ ዞን አስተዳደር ኃላፊን ገድለዋል። በኦሮሚያ ልዩ ዞን ኦነሠ/ኦነግ–ሸኔ ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች በአካባቢው ከመንግስት ታጣቂዎች ወይም ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ብዙ ጊዜ የሚዋጉ ቢሆንም በዞኑ የኦሮሞ አስተዳደር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እምብዛም የተለመደ አይደለም (ለተጨማሪ መረጃ የሰሜን ሸዋን እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ግጭት ገፅን ይመልከቱ)።
በትግራይ ክልል ተጨማሪ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመለሱ
በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ግጭትን ተከትሎ በትግራይ ክልል ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆች የይገባኛል ጥያቄ ወደሚነሳባቸው አካባቢዎች መመለሳቸውን ቀጥለዋል። ባለፈው ሳምንት ወደ 5,000 የሚጠጉ ሰዎች ወደ ሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን ፀለምቲ ወረዳ ተመልሰዋል።3አዲስ ስታንዳርድ፣ ‘ኢትዮጵያ፡ ወደ 5,000 የሚጠጉ ተፈናቃዮች ወደ ሰሜን ምዕራብ ትግራይ ተመለሱ፣’ ሰኔ 29, 2016 የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ከተጀመረ ብዙም ሳይቆይ ጅምሮ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች በአማራ ክልል ቁጥጥር ስር ናቸው። ተፈናቃዮቹ የተመለሱት የአማራ አስተዳደር ከፀለምቲ ወረዳ ከተወገደ በኋላ ነው።
ከየካቲት ወር ጀምሮ በደቡብ ትግራይ ዞን — የይገባኛል ጥያቄ ከሚነሳባቸው አካባቢዎች አንዱ — በትግራይ እና በአማራ ክልል ታጣቂዎች መካከል ውጊያ በተደጋጋሚ ተከስቷል። በሰኔ ወር የትግራይ ኃይሎች ወደ ፀለምቲ ወረዳ መንቀሳቀስ ቢጀምሩም ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር ከተመመካከሩ በኃላ አካባቢውን ለቀው ወጥተዋል። ሰኔ 27 ቀን በተካሄደው የፓርላማ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ የይገባኛል ጥያቄ ወደሚነሳባቸው አካባቢዎች በመመለስ ረገድ ተግዳሮቶች እንዳሉ በማመላከት ነገር ግን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ችግሮችን እንደሚፈታ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።4አዲስ ስታንዳርድ፣ ‘ዜና፡- “ጅምላ ግድያ አንፈፅምም” – ጠ/ሚ አብይ አህመድ የመንግስት ኃይሎች የጅምላ ግድያ ውንጀላ አስተባብለዋል፣’ ሰኔ 27, 2016
ተፈናቃዮች የይገባኛል ጥያቄ ወደሚነሳበት ወደ ፀለምቲ አካባቢ በሰላም መመለሳቸው ጥሩ ማሳያ ቢሆንም የትግራይ ተወላጆች በአማራ መራሹ አስተዳደር ስር የሚገኘው ወደ ምዕራብ ትግራይ ዞን መመለስ ግን የበለጠ ከባድ ስራ ሊሆን ይችላል። የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በተቀሰቀሰበት ወቅት ከ600 በላይ የአማራ ብሔር ተወላጆች በምዕራብ ትግራይ ማይካድራ በምትባል ትንሽ ቦታ ሳምሪ በተባለ የትግራይ ወጣቶች ቡድን ተገድለዋል። በምዕራብ ትግራይ ዞን ከአማራ አስተዳደር ጋር ግንኙነት ያላቸው የታጠቁ ታጣቂዎች ከወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ኮሚቴ5በ2007 ዓ.ም የአማራ አክቲቪስቶች የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ኮሚቴን የመሰረቱ ሲሆን ከ2007 እስከ 2010 በየትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር የሚመራው መንግስት ላይ ተቃውሞዎችን በመምራት ይታወቃል። ኮሚቴው በትግራይ ክልል ባለስልጣናት በሚተዳደረው የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች ውስጥ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆችን ጥቅም ለማስከበር ይፈልጋል። ጋር የተቆራኙ ሲሆን የምዕራብ ትግራይ ዞንን ሁኔታ ለመፍታት ህዝበ ውሳኔ እንዲሰጥ መንግስት ያቀረበውን ሃሳብ ይቃወማሉ።6ኢዮብ ትኩዬ, ‘የራያ ጉዳይ በሕገ መንግሥቱ ይታያል መባሉን እንደሚቃወም የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ገለጸ፣’ ታህሳስ 22, 2016
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሞትን ያስከተለ ጥቃት ደረሰ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ማረቆ ልዩ ወረዳ ፉቶ በተባለ ቦታ ማንነቱ ያልታወቀ ታጣቂ ቡድን ሰኔ 25 ቀን አራት ሰዎችን ገድሎ ሌሎች አራት ሰዎችን አቁስሏል። ጥቃቱ በዞኑ በሚገኙ ዘጠኝ ቀበሌዎች ላይ ከሚነሳ ባለቤትነት ጉዳይ ጋር ተያይዞ በመስቃንና በማረቆ ብሔረሰቦች መካከል ካለው አለመግባባት ጋር የተያያዘ ነው። ሐምሌ 5 ቀን 88 ሰዎች በመስቃን ልዩ ወረዳ በተፈጠረ ግጭት ላይ ተሳትፈዋል በሚል ታስረዋል። ይህ እስር ሐምሌ 1 ቀን ብሔርን መሰረት ያደረገ ጥቃት በማረቆ ወረዳ ከተፈፀመ በኃላ የተደረገ ሲሆን በዚህ ጥቃት ቢያንስ አራት ሰዎች መሞታቸው ታውቋል።
ኢትዮጵያ በጨረፍታ
ሰኔ 22–28, 2016
ይህ መረጃ/ዳታ ከሰኔ 22 እስከ 28, 2016 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
የኩነት አይነቶች
ውጊያዎች: 25 ኩነቶች
ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 0 ኩነት
ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 9 ኩነቶች
የአመፅ ግጭት: 0 ኩነት
ሰልፎች: 0 ኩነት
ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 1 ኩነት