የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት ውስጥ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች መንግስታት በፀጥታ ዘርፍ የሚውስዱትን እርምጃዎችን ያጠናከሩ ሲሆን ይኽውም አዲስ የሰዓት እላፊ መጣልን እና አማፂዎችን ኢላማ ያደረጉ ወታደራዊ ዘመቻዎችን ማስፋፋትን ይጨምራል።
የአማራ ክልል ባለስልጣናት ለፀጥታ ችግር የሰጡት ምላሽ
የአማራ ክልል ባለስልጣናት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተደረጉ ውጊያዎችን ምክንያት በማድረግ በክልሉ እየጨመረ የመጣውን የደህንነት እጦት በማስመልከት ባለፈው ሳምንት ምላሽ ሰጥተዋል። ሐምሌ 21 ቀን የባህርዳር ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት አዲስ የሰዓት እላፊ ያወጀ ሲሆን በዚህም ከምሸቱ ሦስት ሰዓት በኋላ ፍቃድ ከተሰጣቸው ሰዎች ውጪ በከተማዋ ውስጥ የሚደረግን እንቅስቃሴ ከልክሏል። የፀጥታ ምክር ቤቱ በከተማዋ ውስጥ መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስንም ከልክሏል። ከክልከላው አንድ ቀን ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በባህርዳር ከተማና አካባቢዋ ማንነታቸው ካልተገለፀ ግለሰቦች ብዙ መሳሪያዎችን መያዙን አስታውቆ ነበር። በተመሳሳይ የመንግሥት ኃይሎች በደቡብ ጎንደር ዞን ምስራቅ እስቴ ወረዳ በፋኖ ታጣቂዎች ላይ ዘመቻ ማካሄዳቸውን ገልፀዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ሐምሌ 24 ቀን ስብሰባ በካሄደበት ወቅት በክልሉ ከአንድ ዓመት በፊት የተከሰተው የፀጥታ ቀወስ ከጀመረበት ጀምሮ ወደ 7000 የሚሆኑ ታራሚዎች ከ10 ማረሚያ ቤቶች ማምለጣቸው ተገልጧል።1ሲሳይ ሳህሉ፣ ‘በአማራ ክልል ሰባት ሺሕ ታራሚዎች ከማረሚያ ቤት መበተናቸው ተገለጸ፣’ የኢትዮጵያ ሪፖርተር፣ ሐምሌ 24, 2016 የፋኖ አመፅ በመላው የአማራ ክልል እየተስፋፋ ሲመጣ የፌዴራል መንግሥት ሐምሌ 28, 2015 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል። መንግሥት ከ266 የክልሉ ወረዳዎች መካከል ከስምንቱ በስተቀር ሁሉንም የተቆጣጠረ መሆኑን ከገለፀ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰኔ 2016 አብቅቷል። ይሁንና መንግሥት ከተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ያመለጡትን ሰዎች እንደገና መያዝ ያልቻለ ይመስላል። የፀጥታ ሁኔታን ማጠናከር እና የወታደራዊ ዘመቻዎች መቀጠላቸው በክልሉ የቀጠለውን የፀጥታ ችግር ያሳያል። ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት ለተለያዩ የስራ ኃላፊዎች እና የባንክ ኃላፊዎች ባደረጉት ንግግር መንግሥት በአማራ ክልል ከሚገኙ አንዳንድ የታጠቁ ቡድኖች ጋር እየተነጋገረ መሆኑን የገለፁ ቢሆንም ቢያንስ አንድ የፋኖ ቡድን ጉዳዩን አስተባብሎታል።2አዲስ ስታንዳርድ፣ ‘ኢትዮጵያ: ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ ከታጠቁ ቡድኖች ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑን እና ከትግራይ ኃይሎች ብዙ ትንኮሳዎች መኖራቸውን ተናገሩ ፣’ ሐምሌ 26 2016፤ የኢትዮጵያ ሚዲያ ሰርቪስ፣ ‘ኢኤምኤስ እለታዊ ለጠሚሩ የኦነሠ-ኦነግ እና የፋኖ ምላሸ እሁድ ሐምሌ 27, 2016፣’ ሐምሌ 27, 2016
በኦሮሚያ ክልል በሌላ ስኳር ፋብሪካ ላይ የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ጥቃት
በኦሮሚያ ክልል በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሠ) — በመንግሥት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ተብሎ የሚጠራ — እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች የቀጠሉ ሲሆን በምስራቅ ወለጋ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ሰሜን ሸዋ እና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች ውጊያዎች መደረጋቸው ተዘግቧል። ሐምሌ 20 ቀን ኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ በምስራቅ ሸዋ ዞን አራት የመተሃራ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞችን ማገቱ ተዘግቧል። በየካቲት 2015 በፋብሪካው ተመሳሳይ ክስተት የተከሰተ ሲሆን የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች በፋብሪካው ላይ ጥቃት በፈፀሙበት ወቅት አራት ሠራተኞች መገደላቸው ተዘግቦ ነበር።
የስኳር ፋብሪካዎች፣ የማዕድን ማውጫ ስራዎች እና ሌሎች ትላልቅ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በተደጋገሚ የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ አባላት በአብዛኛው ኢላማ ሆነው ቆይተዋል።በሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞን የሚገኘው የፍንጫ ስኳር ፋብሪካ በኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ጥቃት ምክንያት የካቲት 2014 ምርት ለማቆም ተገዶ የቆዬ ሲሆን በቅርቡ ሰኔ 2016 በሙሉ አቅም እንደገና ምርት ማምረት ጀምሯል። በዚህም ምክንያት ፋብሪካው 4 ቢሊዮን የሚገመት ብር (ወደ 50 ሚሊዮን የዩኤስ ዶላር አካባቢ) ኪሳራ ደርሶበታል።3ፋሲካ ታደሰ, ‘የኢትዮጵያ የስኳር ፋብሪካ በታጣቂዎች የተጸፀመን ጥቃት ተክትሎ ሥራ አቆመ፣’ ብሉምበርግ፣ የካቲት 7, 2014፤ ቪኦኤ አማርኛ፣ ‘ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ በጸጥታ ችግር ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት ደርሶብኛል አለ፣’ ሰኔ 4, 2016
በሌላ በኩል የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔን ኢላማ ያደረገ ትልቅ ዘመቻ በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ መጀመራቸውን አስታውቋል። በአካካቢው ምንጮች መሠረት በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን የስኳር ፋብሪካ ሠራተኞችን ጭምር መንግሥት ኦነሠ/ኦነግ-ሸኔን ለመመከት በግዴታ ላይ የተመሠረተ ወታደራዊ ምልመላ እና ሰልጠና እየተደረገ መሆኑ ታውቋል።4ዋዜማ፣ ‘ጋቸነ ሲርና! የኦሮሚያ ክልል መንግስት የአካባቢ ፀጥታ ዘብ “በግዳጅ” እየመለመለና እያሰለጠነ ነው፣”’ ሐምሌ 24, 2016
ኢትዮጵያ በጨረፍታ
ሐምሌ 20-26, 2016
ይህ መረጃ/ዳታ ከሐምሌ 20 እስከ 26, 2016 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
የኩነት አይነቶች
ውጊያዎች: 26 ኩነቶች
ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 1 ኩነት
ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 8 ኩነቶች
የአመፅ ግጭት: 1 ኩነት
ሰልፎች: 1 ኩነት
ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 0 ኩነት