የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በአማጺ ቡድኖች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች ቀጥለዋል። በተጨማሪም በመንግሥት ወታደሮች እና ከመንግሥት ተቃራኒ በተሰለፉ ኃይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንደቀጠለ ነው። በዚህም ምክንያት ባለፈው ሳምንት የፖለቲካ ግጭት ብዛት በአጣቃላይ ጭማሪ አሳይቷል። ይህ በአንዲህ እንዳለ በትግራይ ክልል ውዝግብ በሚነሳባቸው ግዛቶች ውስጥ ውስን ውጊያዎች ካለው የፖለቲካ ውጥረት ጋር ቀጥለዋል።
በኦሮሚያ ክልል የሚደረጉ ውጊያዎች እና ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች
በኦሮሚያ ክልል በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ) — በመንግሥት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ተብሎ የሚጠራው — መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች ተባብሰው ቀጥለዋል። ባለፈው ሳምንት በሆሮ ጉድሩ ወለጋ እና በሰሜን ሸዋ ዞኖች ውጊያዎች የተመዘገቡ ሲሆን ከእነዚህ ውጊያዎች አብዛኛዎቹ የተከሰቱት በሰሜን ሸዋ ዞን ሂደቡ አቦቴ ወረዳ ውስጥ ነው። ከየካቲት 7 ቀን ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት በሂደቡ አቦቴ ወረዳ ኮቤ ጎዴ ቀበሌ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ መካከል በተደረገ ውጊያ ቢያንስ ስምንት ስዎች እንደተገደሉ ተዘግቧል። የካቲት 10 ቀን በሂደቡ አቦቴ ወረዳ በኤጀሬ ከተማ በሁለቱ ወገኖች መካከል በተደረገ ውጊያ ሌሎች ሰባት ሰላማዊ መገደላቸው ተዘግቧል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በኋላ ላይ ባወጣ መግለጫ ሠራዊቱ በሰሜን ሸዋ ዞን አቦቴ ወረዳ ፊቼ አቅራቢያ በኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ላይ በወሰደው ወታደራዊ እርምጃ ስምንት የቡደኑ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ በደርዘን የሚቆጠሩ ታጣቂዎችን መግደሉን ገልጿል።1የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) መከላከያ ሠራዊት፣ ‘ሀገረ ጠል በሆኑ ፅንፈኞች ላይ የሚወሠደው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለፀ፣’ የካቲት 12, 2016
የካቲት 11 ቀን ከኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆናቸው የሚጠረጠሩ ታጣቂዎች በምስራቅ ሸዋ ዞን ከቢሾፍቱ ከተማ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ 30 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በሚኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ዝቋላ ገዳም ላይ ጥቃት በመፈፀም ሰዎችን አፍነው ከወሰዱ በኋላ አራት የቤተ-ክርስቲያኒቱን መነኮሳትን ገድለዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን አመራሮች ለግድያው በተለይም ኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ላይ በማነጣጠር “ታጣቂ ቡድኖችን” ወቅሳለች።2የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ‘በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተላለፈ መልዕክት፣’ የካቲት 14, 2016፤ ቢቢሲ አማርኛ፣ ‘በዝቋላ ገዳም 4 መነኮሳት በታጣቂዎች እንደተገደሉባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አስታወቀች፣’ የካቲት 15, 2016 የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ — በሚያዚያ 2011 ኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ተገንጥሎ የወጣበት ፓርቲ — ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ አጥብቆ ጠይቋል።3የኦሮሞ ነጻነት ግንባር-ኦነግ፣‘ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ካህናት ግድያን አስመልክቶ ጉዳዩ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ የተሰጠ የኦነግ መግለጫ፣’ የካቲት 17, 2016 በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዓመታት ውስጥ ስእዎችን አፍኖ መውሰድ እና የማህበረሰብ መሪዎችን እና ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች ትልቅ አሳሳቢ ሆነዋለ (ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦ ሳምንታዊ፡ ጥቅምት 3-9, 2016 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ፡ ጥቅምት 10-16, 2016ን ይመልከቱ)።4ፍሬድ ሀርተር ፣ ‘ይህ ወረርሽኝ ነው’: በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል እየተስፋፋ የመጣው ሰዎችን የማፈን አስከፊ ሁኔታ፣’ ዘ ጋርዲያን፣ የካቲት 15, 2016 በአንዳንድ የኦሮሞ ተወላጆች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አመራር በአማራ እና በትግሬ ተወላጆች የተያዘ እናየኦሮሞ ብሔር በቂ ውክልና የሌለው ተደርጎ በሚትታይበት በምስራቁ የክልሉ ክፍል የብሔር ይዞታ ያለው ኃይማኖትን መሠረት ያደረገ ጥቃት እየጨመረ የመጣ ችግር ሲሆን ይህ ደግሞ በየካቲት 2015 አለመግባባቶች እና የኃይማኖት ግጭቶች እንዲፈጠሩ አድርጓል።
አማራ ክልል የተፈፀሙ የአየር ጥቃቶች እና የመንገዶች መዘጋት
ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች የቀጠሉ ሲሆን በአዊ፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ምዕራብ ጎጃም እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች ውጊያዎች ተመዝግበዋል። የካቲት 11 ቀን በሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃን ወደራ ወረዳ ውስጥ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መከከል ውጊያ ከተደረገ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በተፈፀመ የአየር ጥቃት በወረዳው ውስጥ በመጓዝ ላይ በነበረ የጭነት ተሽከርካሪ ተመቷል። በጥቃቱ ቢያንስ 30 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ተጨማሪ 15 ሰዎች ቆስለዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ምንጮች በአካባቢው በተደረገ ውጊያ በርካታ የፋኖ ታጣቂዎች መገደላቸውን እና መያዛቸውን ገልፀዋል።5የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት፣ ‘ሠላም ጠል በሆኑ የታጠቁ ሃይሎች ላይ የሚወሠደው ርምጃ ተጠናክሮ ቀጥሏል፣’ የካቲት 14, 2016
ይህ በእንዲህ እንዳለ የካቲት 14 ቀን በሰሜን ሸዋ ዞን በሸዋ ሮቢት ከተማ የፋኖ ታጣቂዎች የኦሮሚያ ልዩ ዞን የአስተዳደር ማዕከል ወደ ሆነችው ከሚሴ ከተማ በመጓዝ ላይ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቢስ ላይ ስምንት ሰላማዊ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን አስወርደው በመውሰድ ተኩሰው መግደላቸው ተዘግቧል።6አዲስ ስታንዳርድ፣ ‘ዜና: በአማራ ክልል ሸዋ ሮቢት ታጣቂዎች ስምንት ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸውን ተከትሎ ኮማንድ ፖስት እገዳ ጣለ፣’, የካቲት 16, 2016 ግድያው የተከሰተው በአካባቢው ውጊያ እየተደረገ እና መንግሥት በአካባቢው የፋኖ ኃይሎችን ኢላማ በማድረግ ወታደራዊ ዘመቻ በማድረግ ላይ ባለበት ሁኔታ እንዲሁም በቦታው በፋኖ ታጣቂዎች፣ በአማራ ታጣቂዎች እና በኦሮሞ ታጣቂዎች መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች በጨመሩበት ዐውድ ውስጥ ነው። በአማራ ክልል በኦሮሞ ልዩ ዞን እና ሰሜን ሸዋ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች ድንገተኛ የፖለቲካ ግጭቶች የተለመዱ ናቸው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት — በአካባቢው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አተገባበርን ለመከታተል የተቋቋመ — በአካባቢው እየጨመረ የመጣውን ግጭት ለመቆጣጠር ‘በጽንፈኛ ኃይሎች’ ላይ እየተደረገ ያለውን ወታደራዊ ዘመቻ በምክንያትነት በመጥቀስ በደብረ ብርሃን፣ ሸዋ ሮቢት እና ደሴ ከተሞች መካከል ያሉ መንገዶች ዘግቷል።7ለምነው መኮንን፣ ኂሩት መለሰ እና ማንተጋፍቶት ስለሺ፣ ‘ከደብረ ብርሃን ደሴ እና ከደሴ ደብረብርሃን የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋረጠ፣’ ዲደብሊው አማርኛ፣ የካቲት 18, 2016
ባለፈው ሳምንት ከአማራ ክልል ከተወጣጡ ተወካዮች ጋር ውይይት በተደረገበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ መንግሥት ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ያለውን ግጭት በሰላም፣ በእርቅ እና በንግግር ለመፍታት ፍቃደኛ መሆናቸውን አመላክተዋል።8ዓለምነው መኮንን፣ ኂሩት መለሰ እና ማንተጋፍቶት ስለሺ፣ ‘የጠቅላይ ሚንስትሩ የእንታረቅ ጥሪ፣’ ዲደብሊው አማርኛ፣ የካቲት 13, 2016 ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮችን ያለመከሰስ መብታቸውን ማንሳትን ጨምሮ መንግሥት የአማራ ብሔርተኛ ቡድኖች ደጋፊዎች ናቸው ያላቸው ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ እየጨመረ ባለበት ውቅት ይህ ጥሪ በመቅረቡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የተደበላለቁ ምላሾችን አስከትሏል።9ቢቢሲ አማርኛ፣ ‘በአንድ ሳምንት ውስጥ ሦስተኛው የምክር ቤት አባል ያለመከሰስ መብት ተነሳ፣’ የካቲት 16, 2016
የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው የትግራይ ክልል ግዛቶች የቀጠሉ ውጊያዎች
የካቲት 13 ቀን በትግራይ ክልል በደቡባዊ ትግራይ፣ ዛታ ወረዳ የትግራይ ብሔር ታጣቂዎች የአማራ ብሔር ታጣቂዎች ላይ ጥቃት የፈፀሙ ሲሆን ይኽውም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጣልቃ እስኪገባ ድረስ ለአጭር ጊዜ የቆየ ውጊያ ቀስቅሷል። ይህ ውጊያ ባለፈው ሁለት ሳምንት በኮረም ከተማ አቅራቢያ እና በጨርጨር፣ በራያ አላማጣ እና በራያ ባላ ወረዳዎች የካቲት 6 እና 7 በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረጉ ውጊያዎች ቀጣይ ናቸው። እንደ ቀደመው ሳምንት ሁሉ የባለፈው ሳምንት ውጊያ ለአጭር ጊዜ ብቻ የቆየ ሲሆኑ ይተዘገበ ሞት አልነበረም። በዚህ አካባቢ የሚከሰቱ ግጭቶች ጉልህ እንድምታ ያላቸው ሲሆኑ አካባቢው በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳበት እና በመንግሥት እና በትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) መካከል ከተፈረመው ከፕሪቶሪያ ስምምነት ጋርም የተያያዘ እንደመሆኑ መጠን የመስፋፋት እድል አላቸው። በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ትህነግ/ህወሓት እና የኢትዮጵያ መንግሥት “ውዝግብ የተነሳባቸው አካባቢዎችን ጉዳይ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ለመፍታት” ተስማምተዋል።10የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት ‘ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ግጭቶችን በቋሚነት ለማቆም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እና በትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ) መካከል የተደረገ ስምምነት፣’ ጥቅምት 24, 2015 ይሁንና መንግሥት ይካሄዳል ላለው ሕዝበ ውሳኔው ቀነ ገደብ ገና አላስቀመጠም።11ዲስ ስታንዳርድ፣ ‘ዜና: የዲሞግራፊ ለውጥ እየተደረገ ባለበት፣ ማፈናቀል በቀጠለበት በምዕራብ ትግራይ ሕዝበ ውሳኔ ማድረግ የማይቻል ነው: የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣’ የካቲት 5, 2016
ኢትዮጵያ በጨረፍታ
የካቲት 9-15, 2016
ይህ መረጃ/ዳታ ከየካቲት 9-15, 2016 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
የኩነት አይነቶች
ውጊያዎች: 39 ኩነቶች
ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 3 ኩነቶች
ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 13 ኩነቶች
የአመፅ ግጭት: 0 ኩነት
ሰልፎች: 1 ኩነት
ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 0 ኩነት