በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ሰኔ 10, 2014 1እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች: 3,017
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች: 16,579
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ: 7,342
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከሰኔ 4 እስከ 10, 2014 2 በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች: 17
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች: 102
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ: 17
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በጋምቤላ ክልል በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ፣ ጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) እና መንግስት ሃይሎች መካከል ከፍተኛ ጦርነት ተመዝግቧል። ጋምቤላ ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ሲነፃፀር በአገሪቷ አንፃራዊ ሰላም ካላቸው ክልሎች አንዱ ተደርጎ ይወሰዳል። ማክሰኞ ሰኔ 7 ቀን በጋምቤላ ከተማ የጋነግ እና የኦነግ–ሸኔ አባላት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከጋምቤላ ክልል ልዩ ሃይል ጋር ተዋግተዋል። ጦርነቱ ከጠዋቱ 12፡30 እስከ ከሰዓት 3 ሰዓት ድረስ ዘልቋል። የመንግስት ታጣቂዎች ከሰአት በኋላ ከተማዋን መቆጣጠር ችለዋል። ነገር ግን ሳምንቱን ሙሉ የተኩስ ድምጽ መሰማት ቀጥሏል። ማክሰኞ በተፈጠረው ግጭት 11 የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እና ሁለት ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ ቢያንስ 40 ሰዎች መሞታቸው የተዘገበ ሲሆን ከ36 በላይ የጸጥታ ሃይሎች እና ሶስት ሰላማዊ ሰዎች ቆስለዋል። የክልሉ መንግስት ከምሽቱ 2 ሰአት እስከ ንጋቱ 12 ሰአት የሚቆይ የምሽት ሰዓት እላፊ ያወጀ ሲሆን ንፁሀን ዜጎችም በቤታቸው ውስጥ እንዲቆዩም አሳስቧል። በተጨማሪም ኦነግ–ሸኔ ባለፈው ሳምንት በክልሉ ምንጃዋት ከተማ አንድ ካናዳዊ ሰላማዊ ሰው ገድሏል (በጋምቤላ ክልል ውስጥ በቅርቡ ሰለነበረው ጦርነት የበለጠ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦ ሳምንታዊ: ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 3, 2014 ይመልከቱ)።
ሰኔ 7 ቀንም በኦሮሚያ ክልል በቄለም ወለጋ ዞን በደንቢ ዶሎ ከተማ 04 ቀበሌ አካባቢ እና በአንፊሎ ወረዳ ሙጊ፣ በምዕራብ ወለጋ ዞን በጊምቢ ከተማ፣ መንዲ ከተማና በላሎ አሳቢ ወረዳ ኢናንጎ እና በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ ኡላ ካቢ፣ ዲማ ኢጃራ እና ዲማ መንደሮች ኦነግ–ሸኔ ከመንግስት ሃይሎች ጋር ተዋግቷል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ )። በደንቢ ዶሎ ከተማ አማፂ ቡድኑ ‘የፖለቲካ እስረኞችን‘ በመፍታት የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር አውሏል። ከዚህ ውጊያ ጥቂት ቀናት በፊት ሰኔ 4 ቀን ኦነግ–ሸኔ ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስ እና የቀበሌ ታጣቂዎች ጋር በአርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ በሊሙ እና ቲጆ ቀበሌዎች ተዋግተዋል። የሺርካ ወረዳ አስተዳደሪ እና የወረዳው ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነርን ጨምሮ 25 ሰዎች መገደላቸው እና 40 ሰዎች መቁሰላቸው ተነግሯል። በማግስቱ በሽርካ ወረዳ በጋሌማ ጫካ ውስጥ ሁለቱ ወገኖች ተዋግተው ኦነግ–ሸኔ 17 የጸጥታ ሃይሎችን መግደሉን እና 22 ማቁሰሉን ተናግሯል።
በኦሮሚያ ክልል በመንግስት ታጣቂዎች የሚፈጸሙ ከህግ አግባብ ውጪ የሆኑ ግድያዎች ቀጥለዋል። ባለፈው ሳምንት አክሌድ በሰላማዊ ሰዋች ላይ የተሰነዘሩ አራት ጥቃቶችን መዝግቧል። ሰኔ 7 ቀን የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል እንደሆኑ የተገመቱ የክልሉ መንግስት ሃይሎች በምዕራብ ሸዋ ዞን ሳሪቲ ቀበሌ ባሏ የኦነግ–ሸኔ አባል ነው የተባለችን አንዲት ሴት ባሏ የት እንዳለ አልተናገረችም በማለት ደብደበው ክሦስት አመት ልጇ ጋር አስረዋታል። ሰኔ 8 አካባቢ በምስራቅ ሸዋ ዞን ሊበን ጩቃላ ወረዳ ዳላጋላ ጂዳ ቀበሌ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎችን ገድለው የሶስት ሰላማዊ ሰዎች ቤቶችን አቃጥለዋል። ተጎጂዎቹ መንግስትን አይደግፉም፣ አርሶ አደሮችን በማዳበሪያ አከፋፈል ጉዳይ ላይ በመንግስት ላይ ተቃውሞ እንዲያሰሙ አድርገዋል ሲሉ ከሰዋቸዋል። በተመሳሳይ ሰኔ 8 ቀን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በምስራቅ ሸዋ ዞን ጊዳራ ቀበሌ የኦነግ–ሸኔ አባላትን ደብቀዋል በሚል 48 ቤቶችን አቃጥለው በማውደም ቁጥራቸው በውል ያልተገለጸ ሰላማዊ ሰዎችን ገድለዋል። ጥቃቱ ከአንድ ቀን በፊት የዚህ ወረዳ አጎራባች በሆነው በቦሰት ወረዳ በአማፂያኑ እና በመንግስት ሃይሎች መካከል የተካሄደውን ውጊያ ተከትሎ የተፈፀመ ነው። የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል እንደሆኑ የሚገመት የክልሉ መንግስት ታጣቂዎች በምስራቅ ወለጋ ዞን በዋማ ሀጋሎ ወረዳ በጊዮ ከተማ ከ11 ቀበሌዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ኦነግ–ሸኔን ደግፋቹኃል በሚል ደብድበው ያሰሩ ሲሆን በርካታ የሰላማዊ ሰዎች ቤቶችንም አቃጥለዋል። የሰው ህይወት አላለፈም ነገር ግን በድብደባው ከደርዘን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ተጎድተዋል።
ሰኔ 4 ቀን በትግራይ ክልል በደቡብ ትግራይ ዞን ራያ አላማጣ ዋጃ አካባቢ የፋኖ ሚሊሻዎች ወደ አካባቢው ተመልሰው መግባት ጀምረዋል። በዚህ ምክንያት የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) ሃይሎች ከአካባቢው ለቀው ወጥተዋል። በዚህ አካባቢ በብዛት የሚኖሩት የራያ ብሔረሰብ በአጎራባች የአማራ ክልል አስተዳደር ስር መሆን የሚፈልጉ ናቸው። በአማራ ክልል የተካሄደውን “የህግ ማስከበር” ዘመቻ ተከትሎ ሰኔ 1 ቀን የፋኖ ታጣቂዎች አካባቢውን ለቀው በመውጣታቸው የትህነግ/ህወሓት ሃይሎች አካባቢውን ተቆጣጥረው ከብቶችን ዘርፈዋል (ለበለጠ መረጃ የኢፒኦ ሳምንታዊ: ከግንቦት 13 እስከ 19, 2014 ይመልከቱ)፤ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎችም በአማራ ክልል ወደ ሚገኝው ቆቦ ከተማ ተሰደዋል። ሰኔ 8 አካባቢ በምዕራብ ትግራይ ዞን ፀገዴ ወረዳ ከትህነግ/ህወሓት ጋር ግንኙነት አላቸው ለቡድኑም ይሰልላሉ የተባሉ 33 ሰዎች በጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፀገዴ ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት አስታውቋል። ከጥቅምት 2013 ጀምሮ የምዕራብ ትግራይ ዞን የሚተዳደረው በአማራ ክልላዊ መንግስት ነው (ለበለጠ ዝርዝር የኢፒኦ የግጭት ማብራሪ ገፅ የትግራይ ግጭት ገፅን ይመልከቱ)።
በመጨረሻም የአፋር ብሔረሰብ አባላት እና የሶማሌ ብሔር ኢሳ ጎሳ አባላት በኦሮሚያ ክልል በአዳማ ከተማ በሁለቱ ወገኖች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በውይይት ለመፍታት የሰላም ኮንፈረንስ አድርገዋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሰኔ 6, 2014)። በግንቦት ወር ላይ የሶማሌ እና የአፋር ክልል መንግስታት ሃይሎቻቸውን በተደጋጋሚ ግጭት ከሚከሰተባቸው አካባቢዎች ለማስወጣት፣ ህዝባዊ የውይይት መድረኮችን ለማዘጋጀት፣ የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ የመጡበት ቀዬ እንዲመለሱ ለማድረግ እና የግጭቱን መንስኤ በጥልቀት በማጥናት ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ተስማምተው ነበር (የሶማሌ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ፣ ግንቦት 5, 2014)። በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ ለረጅም ጊዜ በዘለቀው ውዝግብ ምክንያት ሁለቱ ክልሎች በተደጋጋሚ ይጋጫሉ (ስለዚህ ግጭት የበለጠ ማብራሪያ ለማግኘት በኢፒኦ የግጭት መገለጫ ገጽ የሚገኘውን የአፋር–ሶማሌ የድንበር ግጭት ገጽን ይመልከቱ)።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ ከህግ አግባብ ውጪ ግድያ በጋምቤላ ክልል
ጋነግ እና ኦነግ–ሸኔ በጋራ ካደረሱት ጥቃት በኃላ የመንግስት ሃይሎች የጋምቤላ ከተማን ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠሩ በኋላ የጋምቤላ ክልል ልዩ ሃይል እንደሆኑ የተገመቱ የመንግስት ሃይሎች በከተማዋ ከ10 ያላነሱ ሰላማዊ ሰዎችን በጥይት ተኩሰው ገድለዋል። ግድያው የተፈፀመው የመንግስት ሃይሎች በከተማው ውስጥ ተደብቀዋል ያሏቸውን የጋነግ እና የኦነግ–ሸኔ አባላትን ለማፈላለግ ቤት ለቤት ባደረጉት ፍተሻ ወቅት ነው። ከተገደሉት መካከል ብዙዎቹ ከኦነግ–ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተከሰሱ ኦሮሞዎች እንደሆኑ ተዘግቧል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ሰኔ 9, 2014)።
ቢያንስ አንድ ሰው በጋምቤላ ከህግ አግባብ ውጪ ሲገደል የሚያሳይ ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ ተሰራጭቷል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እንደገለጸው ከሆነ የቤት ለቤት እስር እና ግድያ የሚያሳዩ ተጨማሪ ቪዲዮዎች ደርሰውታል። የኢሰመኮ ዳይሬክተር የጸጥታ ሃይሎች “ያለ ልዩነት ከሚፈፀም የሃይል እርምጃ እንዲቆጠቡ” ጥሪ አቅርበዋል (ኢሰመኮ፣ ሰኔ 10, 2014)።
በኢትዮጵያ ከህግ አግባብ ውጪ የሚፈፀሙ ግድያዎች ትልቅ ችግር ናቸው። ህዝቡ ለደህንነት ተቋማቱ የሚሰጠውን ድጋፍ ከመቀነስ በተጨማሪ የጸጥታ ሃይሎች ያለ ምንም ቅጣት ሊንቀሳቀሱ እንደሚችሉ እያመላከተ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ እየተንሰራፋ ያለውን ከህግ አግባብ ውጪ የሚፈፀሙ ግድያዎች ለማሳየት ያህል ከመጋቢት 24, 2010 ዓ.ም ጀምሮ አክሌድ የመንግስት ሃይሎች የተሳተፉባቸው 367 በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ የጥቃት ኩነቶችን መዝግቧል። በኢትዮጵያ ከጦርነት ቀጥሎ የመንግስት ሃይሎች የተሳተፉባቸው በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ የጥቃት ኩነቶች የሁለተኝነት ደረጃን ይይዛሉ።
በጋምቤላ የተፈፀመው ድርጊት በመንግስት ሃይሎች ከህግ አግባብ ውጪ ከተፈጸሙ ግድያዎች መካከል የቅርብ ጊዜ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ በርካቶቹ ተቀርፀው በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲሰራጩ ነበር። ሰኔ 11 ቀን ኢሰመኮ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ከኦነግ–ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን ቢያንስ 30 ሰዎችን ሲገድሉ የሚያሳይ ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ እየተሰራጨ መሆኑን እንደሚያውቅ ገልጾ ሙሉ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል (ሮይተርስ፣ ሰኔ 12, 2014)። በዋነኛነት መንግስት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ከኦነግ–ሸኔ ጋር ግንኙነት ባላቸው ግለሰቦች ላይ እየወሰደ ባለው እርምጃ ምክንያት ከየካቲት ወር ጀምሮ በዞኑ ውስጥ የመንግስት ሃይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሰነዘሯቸው ጥቃቶች በከፍተኛ ደረጃ ጨምረዋል። ።
ሆኖም ግን እነዚህ ግድያዎች በተቃውሞ መልክ ከህዝቡ ምላሽ አላገኙም። በርካቶች በማህበራዊ ሚዲያ መደናገጣቸውን ቢገልጹም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከህግ አግባብ ውጪ የሚፈጸሙ ግድያዎችን ከማውገዝ ጋር የተያያዘ ምንም አይነት የተመዘገበ የተቃውሞ ሰልፍ የለም። ይህ የሆነበት ምክንያት በመንግስት ከፍተኛ ቁጥጥር በመኖሩ እና መንግስት ለእንደዚህ አይነት የተቃውሞ ዓይነቶች ትዕግስ ስለሌለው ነው። ልክ በጋምቤላ እንደታየው ከህግ አግባብ ውጪ የሚደረጉ ግድያዎች ብዙውን ጊዜ የሚከሰቱት ከአንድ ጦርነት በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሲሆን የጥቃቱ ተጎጂዎቹም ከታጣቂ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው ይወነጀላሉ። ይህ ማለት ብዙውን ጊዜ ከህግ አግባብ ውጭ የሚፈጸመው ግድያ ከታጣቂ ቡድን ጋር በስህተት ግንኙነት አላቸው ተብሎ በሚታሰብ አናሳ ብሔሮች ላይ ያነጣጠረ ነው – ለምሳሌ በጋምቤላ ክልል ኦሮሞዎች እና በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል የጉሙዝ ተወላጆች ወይም የትግራይ ተወላጆች። ስለሆነም በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙ አናሳ ብሔሮች ከጎረቤቶቻቸው ይልቅ በመንግስትም ሆነ መንግስታዊ ባልሆኑ ሃይሎች የጥቃት ሰለባ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።
ከህግ አግባብ ውጪ የሚፈፀሙ ግድያዎች ከመንግስት ኃይሎች ጋር ብቻ የተያያዙ አይደሉም። እንደ ትህነግ/ህወሓት፣ ኦነግ–ሸኔ፣ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል የሚገኙ ፀረ–መንግስት ታጣቂዎች እና ሌሎችም ያሉ መንግስታዊ ያልሆኑ ታጣቂዎችም በቁጥጥራቸው ስር በሚገኙ ቦታዎች በሚኖሩ አናሳ ብሔረሰቦች ላይ ጭፍጨፋ ፈጽመዋል ተብለው ይወነጀላሉ (ተጨማሪ መረጃ የመተከል ግጭት ገጽን እና የምዕራብ እና ቄለም ወለጋ ግጭት ገጽን በማንበብ ማግኘት ይቻላል)።
ሰላማዊ ሰዎች በመንግስትም ሆነ መንግስታዊ ባልሆኑ ቡድኖች ኢላማ ሲደረጉ ፅንፍ የያዘ የፖለቲካ ምህዳርን ያስከትላል። ውዝግብ ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የመንደር እና ከተሞች ነዋሪዎች ከሁሉም በበለጠ እየተጎዱ ናቸው። አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ ሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተዋናዮች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት የማያደርስ መፍትሄ የሚፈልጉበት ጊዜ ነው።